ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ መሪነቱ ተመልሷል


በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ንግድ ባንኮች ባሲሩ ኦማር እና ሲሞን ፒተር ባስቆጠሯቸው ግቦች ሻሸመኔ ከተማን 2-1 ረተዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሻሸመኔ ከተማ ሲገናኙ ንግድ ባንኮች በስድስተኛው ሣምንት ሀዋሳ ከተማን 3-0 ሲያሸንፉ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ በወልቂጤ ከተማ 1ለ0 ተሸንፈው በመጡት ሻሸመኔዎች በኩል ግን የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል። በዚህም ቻላቸው መንበሩ ፣ ምንተስኖት ከበደ ፣ ሄኖክ ድልቢ እና ሀብታሙ ንጉሤ በ ጌትነት ተስፋዬ ፣ ያሬድ ዳዊት ፣ ማይክል ኔልሰን እና ሙሉቀን ታሪኩ ተተክተው ገብተዋል።

ቀን 9 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛው ሙሉቀን ያረጋል ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ብዙ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሻሸመኔዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት እና ጥቅጥቅ ብለው መጫዎትን በመምረጥ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የተሳካ የመከላከል አደረጃጀት ማሳየት ሲችሉ ንግድ ባንኮች በአንጻሩ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት ክፍት ቦታዎችን ፍለጋ ሲታትሩ ተስተውሏል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የነበራቸው ንግድ ባንኮች 8ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። ፈቱዲን ጀማል ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ሱሌይማን ሀሚድ በደረቱ ለበረከት ግዛው አመቻችቶ ሲያቀብል ኳሱን ያገኘው በረከትም ኃይል በሌለው ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

በሙሉ የአጋማሹ ደቂቃዎች ተመሳሳይ አጨዋወት እያሳየን የቀጠለው ጨዋታ ሻሸመኔዎች 18ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን ሲያደርጉ አለን ካይዋ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ሲወጣበት 45ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ንግድ ባንኮች ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው በረከት ግዛው ከቅጣት ምት ባሻገረው ኳስ ፈቱዲን ጀማል በግራ እግሩ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ ንግድ ባንኮች ሲሞን ፒተር እና ፉዓድ ፈረጃን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው የሻሸመኔን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ለመስበር ጥረት ሲያደርጉ ይህ ጥረታቸውም 60ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ሱሌይማን ሀሚድ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ በግራ እግሩ ያሻገረውን ኳስ ባሲሩ አማር ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ በድንቅ አጨራረስ ግብ አድርጎታል። ንግድ ባንኮች ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሱሌይማን ሀሚድ ከተመሳሳይ ቦታ ላይ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሲሞን ፒተር በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ይዞበታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ከነበራቸው ጥቅጥቅ ብሎ የመከላከል አጨዋወት በመውጣት የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት ተጭነው መጫወት የጀመሩት ሻሸመኔዎች 71ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ፈቱዲን ጀማል ቻላቸው መንበሩ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አጥቂው አለን ካይዋ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁንን በግራ ጥሎ በቀኝ በኩል መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ጨዋታው ይበልጥ እየተጋጋለ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ብርቱ ፉክክር ተደርጎበታል። ሆኖም ንግድ ባንኮች 82ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ወደ መሪነት ተመልሰዋል። ሲሞን ፒተር ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ለመቆጣጠር ሲሞክር ቢረዝምበትም በድጋሚ ከግብ ጠባቂው ቀድሞ አግኝቶት ግብ አድርጎታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በመልሶ ማጥቃት ሊጫወቱ እንደሞከሩ በመግለጽ ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት ያስፈልጋቸው እንደነበር ሲናገሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው ጨዋታውን እንደጠበቁት ማግኘታቸውን እና በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው መቅረባቸውን ጠቁመው የሊጉ መሪ መሆናቸው ለተሻለ ተነሳሽነት እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።