መረጃዎች| 26ኛ የጨዋታ ቀን

የሰባተኛው ሳምንት መገባደጃ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሻሸመኔ ከተማ

በውድድር ዓመቱ ሽንፈት ያላስተናገደ እና ድል ያልቀናው ቡድን የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገው ነጥባቸውን ወደ አስራ አራት ከፍ ያደረጉት ንግድ ባንኮች የተነጠቁትን መሪነት ለመመለስ ሻሸመኔ ከተማን ይገጥማሉ።ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ ምንም ሽንፈት ያልገጠመው ብቸኛ የሊጉ ክለብ ነው፤ አራት ጨዋታዎች አሸንፎ በሁለቱም አቻ ተለያይቷል። በጊዜ ሂደት የጎለበተው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወትም የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ነው። ቡድኑ በሊጉ ጅማሮ በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ አስቆጥሮ ሊጉን ቢጀምርም ከዛ በኋላ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች አስቆጥሯል፤ ይህም የማጥቃት ክፍሉ መሻሻል ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በነገው ዕለትም በጨዋታ በአማካይ 1.5 ግቦች ላስተናገደው የሻሸመኔ የተከላካይ ክፍል ትልቅ ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል። በነገው ዕለትም በድጋሜ ወደ መሪነት ለመመለስ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ ውጭ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠማቸው ሻሸመኔዎች በአንድ ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል፤ በነገው ዕለትም የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ባንክን ይገጥማሉ። ሻሸመኔዎች የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላም በአጨዋወትም ሆነ በቋሚ አሰላለፍ ብዙም ለውጥ አላደረጉም፤ የነገው ዕለት ላይ ግን የአሰልጣኝ ዘማርያም ሁለተኛ ጨዋታ እንደመሆኑና እንዲሁም አሰልጣኙ የተሻለ የመዛጋጃ ጊዜ አግኝተው የሚያደርጉት ግጥምያ ስለሆነ ከባለፈው ጨዋታ ለውጦች የሚኖርበት ዕድል የሰፋ ነው። በተለይም በሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ክፍልና በቀዳሚነት ለውጥ ሊደረግበት የሚገባ ክፍል ነው።

ንግድ ባንኮች በጉዳትና በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በሻሸመኔ በኩል ግን ያሬድ ዳዊት በዚህ ጨዋታ ተሳትፎ አይኖረውም።

ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

ተመሳሳይ አምስት ነጥቦች ሰብስባው በግብ ክፍያ የሚበላለጡ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ከተከታታይ የአቻና የሽንፈት ውጤቶች በኋላ ሻሸመኔ ከተማን አሸንፈው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸው ያገኙት ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ሲገጥማቸው ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አቻ ተለያይተው ወደ ዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ። ሲዳማ ቡናዎች ውጤታማ ያልሆነ የማጥቃት ክፍል አላቸው፤ በሊጉ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎችም በአራቱ ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል። ይህ ቁጥርም ቡድኑ ምን ያህል ደካማ የማጥቃት ክፍል እንዳለው ማሳያ ነው። ቡድኑ ጨዋታዎችን ለማሸነፍም ይህንን ችግር መቅረፍ ይጠበቅበታል፤ ሲድማዎች ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የነበራቸው እጅግ ዝግ ያለ የማጥቃት ሽግግር ውጤታማ አላደረጋቸውም። በአጨዋወቱ ይህ ነው የሚባል የጠራ ዕድልም አልፈጠሩም፤ በረዥም ጊዜ ጉዳት የነበረው አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ከጉዳት ተመልሶ ጨዋታ መጀመሩም ጎል ለተራበው ቡድን ትልቅ ዜና ነው።


ለአምስት ተከታታይ ሳምንታት የሽንፈትና የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከድል ጋር የተራራቁት ድሬዳዋ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ብያደርጉም ጥረቱ ሙሉ ሦስት ነጥብ አላስገኘላቸውም። ብርቱካናማዎቹ ምንም እንኳ በመጨረሻው ጨዋታ ከንግድ ባንክና አዳማ ከተማ ካጋጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት አገግመው አቻ ቢለያዩም ተከታታይ ድል አልባ ጉዟቸው ግን መግታት አልቻሉም። ብርቱካናማዎቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በአማካይ ሁለት ግቦች አስተናግደዋል፤ ከዛ በተጨማሪ በውድድር ዓመቱ በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው ግባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡበት። እነዚ ቁጥሮችም የቡድኑ የመከላከል ድክመት ማሳያዎች ናቸው፤ አሰልጣኝ አስራት አባተም በቅድምያ ማስተካከያ የሚፈልገውን የተከላካይ ክፍል ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሌላው ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያሳዩት ተስፋ ያለው የማጥቃት እንቅስቃሴም ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።

ድሬዳዋ ከተማዎች ያሲን ጀማል፣ አብዩ ካሳዬና ኤፍሬም አሻሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።