የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የ4ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ልደታ ክ/ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ድል አድርገዋል።

ረፋድ አራት ሰዓት መካሄድ በጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የቀን ሁለት መርሃ ግብር ልደታ ክፍለ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ አገናኝቶ ልደታ 2ለ1 አሸንፏል። እምብዛም የግብ ሙከራም ሆነ ጥሩ እንቅስቃሴ ባልታየበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽን ግብ እስከተቆጠረባቸው ደቂቃ ድረስ ድሬዳዋ ከልደታ አንፃር ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ችለዋል። ሆኖም ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ልደታዎች ነበሩ። ገና እረፍት ሳይወጡ የተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉት ልደታዎች ቅያሬያቸው ፈጣን ፍሬ አፍርቶ የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ሲቀር ተቀይራ በገባችው ማንአዩሽ ተስፋዬ ከርቀት መጥታ ባስቆጠረችው ግብ እረፍት 1ለ0 እየመሩ መውጣት ችለዋል።

ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ወደጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች የፊት መስመር ተጫዋቾች በሆነችው በቃልኪዳን ጥላሁን አማካኝነት በ55ኛው ደቂቃ የቆመ ኳስ በርቀት በማስቆጠር አቻ እንዲሆኑ አስችላለች። አንድ እኩል በሆነ ውጤት መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ልደታዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ማንአዩሽ ተስፋዬ አክርራ በመምታት ወደግብነት ቀይራ ልደታ ክ/ከተማ 2ለ1 አሸንፎ እንዲወጣ አድርጋለች።

ድንቅ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባስመለከተን በቀን 8 ሰዓቱ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማን ከሀዋሳ አገናኝቶ በሀዋሳ 1-0 በላይነት ተጠናቋል። ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎች በታዩበት እና የሁለቱም ቡድን ድንቅ እንቅስቃሴ በታየው በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በተደጋጋሚ ወደተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል በመሄድ የግብ ሙከራዎችን ሲያደረጉ ተስተውለዋል።

የመጀመሪያ የጨዋታ ክፍለ ግዜ ላይ በተደጋጋሚ የሀዋሳ አጥቂ መስመር ተጫዋቾች የአርባምንጭ ከተማ በረኛ ላይ ፈታኝ የሆኑ የግብ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን በጨዋታው ጎልታ መውጣት የቻለችው ቱሪስት ለማ እና እሙሽ ዳንኤል ከርቀት እና በእርስ በእርስ ቅብብሎሽ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል። አርባምንጭ ከተማ በበኩላቸው በአጥቂያቸው ፎዚያ መሐመድ አማከይነት የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግ ጥሩ ሆኖ የዋለውን የሀዋሳ ከተማን የተከላካይ መስመር ክፍል ጥሶ መግባት ተስኗቸው እረፍት 0ለ0 በሆነ ውጤት ወጥተዋል።

በሁለተኛ አጋማሽ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ተሽሎ የገባው የሀዋሳ ከተማ ቡድን ሁለተኛ አጋማሽ ገና ከመጀመሩ በ49ኛው ደቂቃ የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጭ መስሎቸው በተዘናጉበት አጋጣሚ ቱሪስት ለማ ከበረኛ ጋር ተገናኝታ ኳስና መረብን በማገናኘት የጨዋታውን ብቸኛ ጎል በስሟ አስመዝግባለች። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ግዜ በአርባምንጭ ከተማ በኩል የግብ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን ሀዋሳ ከተማም በአንፃሩ ተጨማሪ ግቦችን ሲያደረግ ተመልክተናል።

10:00 ሰዓት ቅ/ጊዮርጊስን ከአዲስአበባ ከተማ ያገናኘው መርሃ ግብር በአዲስአበባ ከተማ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ በላይነት ያሳየው የአዲስአበባ ከተማ ቡድን ጨዋታ በጀመረ በ13ኛው ደቂቃ በአይናለም ዓለማየሁ አማካኝነት በእርስ በእርስ ቅብብሎሽ በተገኘው ግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደተቃራኒ ቡድን በሚሄዱበት አጋጣሚ የአዲስአበባ ከተማ ተከላካዮች ኳሱን በማስጣል በመልሶ ማጥቃት በ19ኛው ደቂቃ በየምስራች ሞገስ አማካኝነት ግቅ በማስቆጠር እረፍት 2ለ0 እየመሩ ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወደጨዋታው ለመመለስ የተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉት ጊዮርጊሶች ኳስን ይዞ በመጨወት የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። በ53ኛው ደቂቃም በእርስ በርሰሰ ቅብብሎሽ የአዲስአበባ ግብ ክልል በሚገቡበት አጋጣሚ የአዲስአበባዋ ተከላካይ አዳነች ጌታቸው ኳሱን ለማፅዳት በረጅም ለማምጣት ሲትሞክር መሰረት ገዛኸኝ አግንታ ወደግብነት ቀይራለች። የአቻነት ግብ ፍለጋ የአዲስአበባን ግብ ክልል ጥሶ ሲገቡ የተሰተዋሉት ጊዮርጊሶች በ60ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረችዋ መሰረት ገዛኸኝ በርቀት አክርራ የመታችው ኳስ ከመረብ ተገናችቶ 2 አቻ መሆን ችለዋል።

ጨዋታው አቻ ከሆነ በኋላ ጥሩ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ በጨዋታው ጎልታ የታየችው እና የጨዋታው ኮከብ መሆን የቻለችው አምበላቸው አዳነች ጌታቸው በ76ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረላትን ግብ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር አዲስአበባ 3-2 አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ አስችላለች።

በተመሳሳይ 10፡00 ሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ በተደረገ ጨዋታ አዳማ ከተማ ከ ሀምበርቾ 2-2 አቻ ተሌኣይተዋል። ይታገሱ ተገኝወርቅ እና ሳባ ኃይለሚካኤል ለአዳማ ከተማ ሲያስቆጥሩ ብርሃን ኃይለሥላሴ ሁለቱንም የሀምበርቾ ጎሎች አስቆጥራለች።

ሊጉን ከ4 ጨዋታ 10 ነጥብ የሰበሰበው ቦሌ ክ/ከተማ በቀዳሚነት ሲመራ ሎዛ አበራ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ5 ጎሎች የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን ደረጃ እየመራች ትገኛለች።