የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች

ኢትዮጵያ መድን እና ፋሲል ከነማን ተከትለው ወደ ቀጣይ ዙር የሚያልፉ ሁለት ክለቦችን የሚለዩ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች

ባህርዳር ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

በሁለቱም የሊግ እርከኖች በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙ ሁለት ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርቧል።

በሁለተኛው ዙር ፍሬዘር ካሳ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ሸገር ከተማን አንድ ለባዶ አሸንፈው ወደ ቀጣይ ዙር ያለፉት ባህርዳር ከተማዎች የባለፈው ዓመት የአፍሪካ ውድድር ተሳታፊነታቸውን ለማስቀጠል በከፍተኛ ሊጉ በጥሩ አቋም ላይ ያለው አርምንጭ ከተማን ይገጥማሉ። ሦስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ላይ አሸንፈው በጥሩ የአሸናፊነት መንገድ ላይ የሚገኙት ባህርዳር ከተማዎች በመጀመርያው ሳምንት በኢትዮጵያ መድን ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ በሰባት ሳምንታት ሽንፈት አላስተናገዱም።


በሁለተኛው ዙር ኦሮምያ ፖሊስን በመለያ ምት አሸንፈው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት አርባምንጮች በከፍተኛ ሊግ ከመሪው በሁለት ነጥብ ርቀው ይገኛሉ። አርባምንጭ ከተማዎች ከሰባት ጨዋታዎች አስራ አምስት ነጥቦች ሰብስበዋል። በአራት ጨዋታዎች ድል ሲቀዳጁ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ቡድኑ በሰባት ጨዋታዎች አስራ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ያለው ቡድን ነው፤ አራት ግቦች ያስቆጠረው አሸናፊ ተገኝም ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ ነው። ቡድኖች ነገ ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት ዛሬ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ የተገናኙ ሲሆን ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቢሾፍቱ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በነገው ዕለት የሚከናወነው ሁለተኛ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን ሁለት ለአንድ ሀላባ ከተማን ደግሞ በመለያ ምት አሸንፈው ወደዚህ ዙር የበቁት ቢሾፍቱ ከተማዎች በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ከሰባት ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦች ሰብስበዋል። በሊጉ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል፣ በሦስቱ ሽንፈት ሲገጥማቸው በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ቡድኑ አስር ግቦች ስያስቆጥር በአንፃሩ አስር ግቦች ተቆጥረውበታል። በነገው ጨዋታም በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ የማጥቃት ክፍል ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆነውን የአዳማ ከተማ የአጥቂ ክፍል የማቆም ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

በሁለተኛው ዙር ሲዳማ ቡናን አራት ለባዶ አሸንፈው ወደ ቀጣር ዙር ያለፉት አዳማ ከተማዎች በፕሪምየር ሊጉ ካስመዘገቡት ተከታታይ የአቻና የሽንፈት ውጤት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ቢሾፍቱ ከተማን ይገጥማሉ። በሁለተኛው ዙር ሙሴ ኪሮስ፣ መስዑድ መሐመድ፣ ነቢል ኑሪና መሐሪ መና በራሱ ላይ ባስቆጠራት ግብ አማካኝነት በሰፊ ልዩነት ማሸነፍ የቻሉት አዳማዎች ወደ አህጉራዊ ውድድር ለመመለስ የከፍተኛ ሊጉን ተወካይ ይገጥማሉ። ቡድኑ ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያን ወክሎ በሴካፋ የክለቦች ዋንጫ መሳተፉ ይታወሳል።