ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አርባምንጭ ከተማ መሪነቱን ሲያስቀጥል ነጌሌ አርሲም መከተሉን ቀጥሏል

በአስረኛ ሳምንት የከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ለ’በመጀመሪያ ቀን ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው የምድቡ መሪዎች ድል አድርገዋል።

ረፋድ አራት ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማን ከቦዲቲ ከተማ ያገናኘው መርሃ ግብር በአርባምንጭ ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አዞዎቹ በግብ ክፍያ በልጠው የምድብ ለ መሪነታቸውን አስቀጥለዋል።

ቦዲቲ ከተማ ገና ጨዋታ ከጀመረ በ6ኛው ደቂቃ በእርስ በርስ ቅብብሎሽ ሄደው የመጀመሪያ ግብ በሙለለቀን ተስፋዬ አማካኝነት በማስቆጠር መሪ መሆን ችለው ነበር። ሆኖም ግን በመሪነት የቆዩት ለሶስት ደቂቃ ብቻ ነበር። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ገብ ፍለጋ ኳስን ወደፊት ጠፍተው ሲጫዎቱ የተስተዋሉት አዞዎቹ በ9ኛው ደቂቃ በአርባምንጭ ከተማው የተከላካይ መስመር ተጫዋች አበበ ጥላሁን አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ ሆነዋል። አበበ ጥላሁን ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ነው አርባምንጭ ከተማዎችን አቻ ማድርግ የቻለው።

የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ኳስን ተቆጣጥረው በመረጋጋት ሲጫወቱ የተስተዋሉት አዞዎቹ በተደጋጋሚ የተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ጋር ሲደርሱ ተመልክተናል። በ37ኛው ደቂቃ የአርባምንጩ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው አሸናፊ ተገኝ ከእንዳልካቸው መስፊን ጋር በእርስ በርስ ቅብብሎሽ ያገኛት ኳስ ወደግብነት ቀይሮ ዕረፍት እየመሩ እንዲወጡ አስችሏል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ቦዲቲ ከተማዎች ጠንከር ብሎ የተመለሱ ሲሆን የአርባምንጭ ከተማን ግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ጥሩ ሆኖ የዋለውን የአረባምንጭ ከተማን ተከላካይ ክፍል አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። አርባምንጭ ከተማዎችም አለፈው አለፈው የግብ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የፊት መስመር ተጫዋቻቸው አህመድ ሁሴን ሳይጠቀም ቀርቷል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ደቂቃ ውስጥ ተቀይሮ የገባው የአርባምንጭ ከተማ የታደጊ ቡድን ፍሬ የሆነው ተዎድሮስ አጬ ከመስመር የተሻገረለት ግብ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር አዞዎቹ የግብ ልዩነታቸውን አስፍተው 3ለ1 አሸንፈው እንዲወጡ አስችሏል።

ቀን ስምንት ሰዓት ላይ በተደረገ መርሃግብር ነጌሌ አርሲ ከጋሞ ጨንቻ ተገናኝተው ነጌሌ አርሲ በጠባብ ውጤት ተጋጣሚውን ማሸነፍ ችሏል።

ብዙ የግብ ሙከራዎች በታየው በዚህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኞች መካከል ብዙ ግብ የሚሆኑ ኳሶች ሳይጠቀሙ ሲቀሩ መመለከት ተችሏል። ነጌሌ አርሲዎች  በመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ብዙ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የተስተዋሉ ሲሆን ምናልባትም በግብ ክፍያ መስተካከል ምችሉበትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

በ36ኛው ደቂቃ የነጌሌ አርሲው ሙሉቀን ተስፋዬ ከግብ ክልል ውጪ ሆኖ አክርሮ የመታት ኳስ የጋሞ ጨንቻው ግብ ጠባቂ ሲመልስ ኳሷን ሲጠብቅ የነበረው የፊት መስመሩ ተጫዋች ታምራት ኢያሱ ኳስ እና መረብ አገናኝተው ዕረፍት በአርሲ ነጌሌ አንድ ለዜሮ መሪነት ወጥተዋል።

ጋሞ ጨንቻ በአንፃሩ በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብሎ በመግባት የኳስ ብለጫ የወሰደ ሲሆን ብዙ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶችን እምክነዋል። ነጌሌ አርሲዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒ የመከላከል ስልት ይዘው የገቡ ሲሆን አለፈው አልፈውም የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

ሆኖም ግን ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ ግብ ነጌሌ አርሲ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ በግብ ክፍያ ተበልጦ የምድብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው ደሴ ከተማን ከባቱ ከተማ ያገናኘው መርሃ ግብር በባቱ ከተማ በላይነት ሲጠናቀቅ ባቱ ከተማ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

በቀዳሚው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ደሴ ከተማዎች በ10ኛው ደቂቃ በአቡሽ ደርቤ እና በፀጋ ደርቤ በሁለቱ ወንድማማቾች አማካኝነት በእርስ በእርስ ቅብብሎሽ  ወደ ተቃራኒ ቡድን በመሄድ የግብ ሙከራ ያደረጉትን ኳስ የባቱ ከተማው ግብ ጠባቂ መልሶባቸዋል።

በድጋሚም ደሴ ከተማዎች የግብ ሙከራ ያደረጉትን ኳስ ባቱ ከተማ ተከላካዮች አስጥለው በመልሶ ማጥቃት በ15ኛው ደቂቃ ያገኙን ዕድል በመጠቀም በየሺጥላ ድቢ አማካኝነት ኳስና መረብ አጋኝተው ዕረፍት እየመሩ መውጣት ችለዋል።

በሁለቱም አጋማሽም ጥሩ በመንቀሳቀስ የጨዋታ በላይነት እና በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ደሴ ከተማዎች በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። በ50ኛው ደቂቃ በፀጋ ደርቤ ላይ በግብ ክልል ውስጥ ጥፋት ተሰርቶ ፍፁም ቅጣት ምት አግንተዋል። ሆኖም ግን ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት በሱፍቃዱ ነጋሽ አምክኗል።

ጨዋታው እስካለቀ ድረስ የግብ ሙከራዎችን ደሴ ከተማ ሲያድርግ የተመለከትን ሲሆን ዛሬ ጥሩ ሆኖ የዋለው የባቱ ከተማው ግብ ጠባቂ ኢያሱ ተካ ኳሶችን ስመልስባቸው ተስተውሏል። በዚህ መሰረት ጨዋታው ሲፈፀም አሰልጣኛቸው የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኖባቸው በምክትል አሰልጣኞች እየተመሩ የሚገኙት ደሴ ከተማዎች ከተከታታይ ድል በኋላ በጠባብ ውጤት ሽንፊት ሲያስተናግዱ ከተከታታይ ሽንፊት በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ባቱ ከተማ ሦስተኛ ድሉን ከጠንካራው ቡድን ከደሴ ከተማ ሦስት ነጥብ ቀምተዋል።