የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 መቻል

“ጠንካራ ጨዋታ ስለነበር ፣ እነርሱም የመከላከል ሂደታቸው ጠንካራ ስለሆነ በውጤቱ ዕኩል ለዕኩል ወጥተናል” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

“የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ከሽመልስ ይሄን መማር አለባቸው” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ

ሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች ነጥብ በመጋራት ካጠናቀቁት የምሽት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞች ጋር ቆይታን አድርጋለች።


አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ወስደው ስለ ተጫወቱበት ጨዋታ…

“ጨዋታውን ከሽንፈት መጥተን ማድረግ ያለብንን ለመስራት ብዙ ነገሮችን አድርገናል። የተሻለ ነበርን ጥሩ ዕድሎችን አግኝተናል ፣ ቀድሞ ገብቶብን ማግባት እና ወደ ማጥቃት ቦታ ቶሎ ቶሎ እንሄድ ነበረ ጥሩ አጋጣሚዎች ነበሩ ጨዋታው ጠንካራ ስለነበር ዕኩል ለዕኩል ወጥተናል።”

የቅዱስ ጊዮርጊስ በተከላካዮች በመስመር ማጥቃት እንቅስቃሴ መገደቡ ቡድኑ ፈልጎት ወይስ በተጋጣሚ ቡድን ምክንያት …

“አልተገደበም ፤ ምንም የተገደበ ነገር የለም እነርሱ እንደውም ፉል ባኮቻቸው በማጥቃት የሚጫወቱት የመስመር ተጫዋቾቻቸው የእኛን ፉልባኮች ሲያባርሯቸው ነበር። በማጥቃት ክልል ውስጥ ሳይሆን ይሳተፉ የነበረው በመከላከል ውስጥ ነበር። እነርሱ ለመዝጋት ቦታዎቹን ፣ እንደዛም ሆኖ ብዙ ነገሮችን አድርገናል ማድረግ ያለብንን አድርገናል ፣ ጥሩ ነገር ሰርተናል ተጫዋቾቹም ሰርተዋል ብዬ ነው የማምነው ግን ጠንካራ ጨዋታ ስለነበር ፣ እነርሱም የመከላከል ሂደታቸው ጠንካራ ስለሆነ በውጤቱ ዕኩል ለዕኩል ወጥተናል።”

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል

ስለ ሁለቱም አርባ አምስት ደቂቃ…

“ጨዋታው ትንሽ ውጥረት የተሞላበት ነው። ተጫዋቾችም ውጤቱን ስለፈለጉት ኳሱን ቶሎ ቶሎ በመልቀቅ ውጤት ለማምጣት ነበር ጥረት የተደረገው ግን አልተሳካም እና ከቤታችን ይዘን የመጣነውን አንድ አንድ ነጥብ ይዘን ተመልሰናል።”

ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ግብ ማስተናገዳቸው እና ቡድኑ በማጥቃቱ ወይስ በመከላከሉ ጥንካሬው…

“ሁለቱም ሚዛናዊ ነው ፣ እኛ ጋር ሁሌም ጎል የሚገባው ወደ ፊት ስትሄድ ነው ፣ ስትከላከል ደግሞ ትናንሽ ስህተት ከሰራህ ግብ ሊኖርህ ይችላል ፣ ይሄ ነው የተፈጠረው በጣም ቀላል ነገር ነው እናስተካክላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”

ብዙ ዕድል ያለ መፍጠር ድክመት …

“መዳከም አይታይም ፣ እንደዛ ነው የምለው ቅድም ያልኩህ ነው ችኮላዎቹ ናቸው ማጥቃቱን እንዳናደራጅ ያደረገን እና የጊዮርጊስ አግሬሲቭ አጨዋወታቸው ያ ደግሞ እንደፈለክ ኳሱን እንዳታደርግ አድርጎናል እና አንዳንዴ ደግሞ ይሄ ተጫዋቾች ትንሽ እኛ ላይ ጫና ነበረ ቢያንስ ሽመልስ ዛሬ ከብሔራዊ ቡድን ሽኝት የተነሳ ይሄን ጨዋታ አሸንፎ ለእርሱ ማበርከት ይፈልጋሉ ፣ ስለዚህ ያ ጉጉት ነበረባቸው። ጉጉቱ ይበልጥ የፈለግነው ነገር እንዳናደርግ አድርጎና።”

የሽመልስ ከብሔራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉ ለክለቡ ስለ ሚሰጠው ጥቅም…

“በክለቡ ላይ ብቻ ያተኩራል ፣ ሽመልስ እንግዲህ እንደምታውቀው ብዙ ዓመት ተጫውቷል ለብሔራዊ ቡድኑ ፣ እግር ኳስ ስትጫወት በአብዛኛው ችሎታ አይደለም። ችሎታ እግር ኳሱ ጋር ነው የሚያደርስህ ዲሲፕሊን እግር ኳሱ ውስጥ እንድትቆይ ነው የሚያደርግህ ፣ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ከሽመልስ መማር አለባቸው። ሽመልስ እኔ የማከብረው ተጫዋች ነው አሁንም ቡድኑን በብዙ በኩል ይረዳል ፣ ወደፊትም ከክለባችን ጋር መልካም ነገር ይሰራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”