መረጃዎች| 36ኛ የጨዋታ ቀን

በነገው ዕለት የሚካሄዱ የዘጠነኛው ሳምንት ሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች

ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ብርቱካናማዎቹና ዐፄዎቹ የሚያደርጉትን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

በመጨረሻው ሳምንት በባህርዳር ከተማ የሁለት ለአንድ ሽንፈት የገጠማቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በስምንት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ብርቱካናማዎቹ በውድድር ዓመቱ ሁለት ድል፣ አራት ሽንፈትና ሁለት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበዋል፤ የወጥነት ችግርም ከቡድኑ ችግሮች አንዱ ነው። በስምንት ሳምንታት ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ብቻ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ይዘው መውጣታቸውም የዚ ማሳያ ነው።

ቡድኑ ምንም እንኳ የግብ ዕድሎች የመጠቀም ትልቅ ችግር ቢኖርበትም በጨዋታ በአማካይ 1.1 ግቦች ያስቆጠረ የአጥቂ ጥምረት አለው፤ ይህም ከሰንጠረዡ ወገብ በታች ከሚገኙ ክለቦች የተሻለ ቁጥር ነው። ብርቱካናማዎቹ ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው ጨዋታዎች መጠነኛ መሻሻል ማሳየታቸው አይካድም። ሲዳማ ቡናን ሁለት ለባዶ ባሸነፉበት ጨዋታና ከጠንካራው ባህርዳር ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ያሳዩት ተጋድሎም አንዱ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ አስራት አባተ በነገው ዕለት ከስምንቱ ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ግቡን ሳያስደፍር የወጣውና አስር ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል።

ወላይታ ድቻና ሀድያ ሆሳዕናን በገጠሙባቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ዐፄዎቹ በአስራ ሁለት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ዐፄዎቹ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ ከወጣ በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስተናግዶ የወትሮ ጥንካሬውን ካጣው የተከላካይ ክፍላቸው ውጭ በእንቅስቃሴ ረገድ መጥፎ የሚባል ብቃት አላሳዩም። ሽንፈት በገጠሙባቸው ጨዋታዎቹ የነበራቸው የኳስ ቁጥጥርና መሰል ብልጫዎችም የዚ ማሳያ ናቸው። ሆኖም በሁለቱም ጨዋታዎች በተለይም በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት በገጠመባቸው ጨዋታ በቁጥር በዝቶ የተከላከለውን አደረጃጀት ሰብረው የጠሩ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። አሰልጣኝ ውበቱ አባቱ ቡድኑ በሁለት ተከታታይ ሳምንታት ያጋጠመውን ፈተና ለመፍታትም የግብ መገኛ አማራጮቻቸው ማስፋት ይጠበቅባቸዋል። ከዚ በተጨማሪም በተጠቀሱት ጨዋታዎች የቀደመ ጥንካሬውን ያጣው የተከላካይ መስመር ጥገናዎች ይሻል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል ተመስገን ደረስ፣ ዓብዱልፈታህ መሐመድ፣ ያሲን ጀማል በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። የቻርለስ ሙሴጌ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። የፋሲል ከነማን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳትነት በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ሶሬሳ ካሚል የሚዳኙ ይሆናል።

ፋሲል እና ድሬዳዋ በሊጉ እስካሁን 12 ጊዜ ተገናኝተዋል። ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ አምስት ፋሲል ከነማ አራት ድሎችን ሲያሳኩ በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ 27 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ 15 ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 12 ጎሎች አስመዝግበዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ሀይቆቹ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፤ ቡናማዎቹም የደርቢው ድል ለማስቀጠል የሚያደርጉት ፍልምያ የተመለከቱ መረጃዎች

በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደው በመጥፎ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙት ሀዋሳዎች በዘጠኝ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሀዋሳዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች በፊት እንደ ቡድን የሚከላከል ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ነበራቸው፤ በአራት ሳምንታት ግብ ሳያስተናግዱ መዝለቃቸውም የዚ ውጤት ነበር። ሆኖም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ከዚ ቀደም የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን የነበረው ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት ጥንካሬውን አጥቷል፤ በሦስት ጨዋታዎች የተቆጠሩባቸው ስምንት ግቦችም የዚ ማሳያ ናቸው። ሀይቆቹ ከሊጉ ጅማሮ አንስቶ ወጥነት የጎደለው የማጥቃት ክፍላቸው የቡድኑ ዋነኛ ችግር ነው። ቡድኑ በመጀመርያው ሳምንት ፋሲል ከነማ ላይ ሦስት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ላይ ማስቆጠር የቻለው ሦስት ግቦች ብቻ ነው። ይህ ቁጥርም ቡድኑ ምን ያህል ግብ የማስቆጠር ችግር እንዳለበት ማሳያ ነው፤ አሰልጣኝ ዘርአይ ቡድኑ ዳግም ወደ እሸናፊነት እንዲመለስ በተለይም በፊት መስመሩ ላይ ያለው ድክመት ማሻሽል ይኖርበታል።

ከተከታታይ አምስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ነጥባቸው ወደ አስራ አንድ ከፍ ያደረጉት ቡናማዎቹ ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻሉ ወደ ሰንጠርዡ ሽቅም የሚወጡበት ዕድል አግኝተዋል። ቡናማዎቹ በመጀመርያዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ ከወጡ በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች አስር ግቦች በማስተናገድ መጥፎ የመከላከል ቁጥሮች አስመዝግበዋል። ሆኖም በአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ስር ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታ ከአምስት ሳምንታት በኋላ መረባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል። ቡድኑ የሊጉን ጠንካራ የማጥቃት ጥምረት የመከተበት መንገድም በአሰልጣኙ ስር ከታዩ በጎ ጎኖች አንዱ ነው፤ በመጀመርያው ጨዋታቸው በአመዛኙ ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የተከተሉት አዲሱ አሰልጣኝ በነገው ጨዋታ ግን በውስን መልኩ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሰልጣኙ የመጀመርያው ጨዋታቸው ደርቢ መሆኑና ጨዋታውን ቀድመው መምራት መጀመራቸው ቡድኑ ጥንቃቄ መርጦ እንዲጫወት አስገድዶታል፤ ይህንን ተከትሎም በነገው ጨዋታ ውስን የአጨዋወት ለውጥ ይኖራል ተብሎ ይገመታል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ከአጥቂው ሙጂብ ቃሲም ውጭ ሙሉ ቡድን ለጨዋታው ዝግጁ ነው፤ በኢትዮጵያ ቡና በኩል የረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው ሮቤል ተክለ ሚካኤል በተጨማሪ ሬድዋን ናስርም በነገው ጨዋታ አይሰለፍም።

በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው፤ ረዳቶቹ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ወጋየሁ አየለ ከአራተኛ ዳኛው ባሪሶ ባላንጎ ጋር በጣምራ ይዳኙታል።

በሊጉ የሁሉም ዓመታት ተሳትፎ ሪከርድ ያላቸው ክለቦቹ ነገ ለ49ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። ቡና 15 ሀዋሳ ደግሞ 16 ጊዜ ድል ሲያደርጉ 17 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 56 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 51 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።