ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አርባምንጭ ከተማ መሪነቱን አስቀጥሏል

በምድብ ‘ለ’ 12ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን መርሃ ግብር መሪው አርባምንጭ ከተማ መሪነቱን ሲያስቀጥል ባቱ ከተማ ፣ ነጌሌ አርሲ እና ቦዲቲ ከተማም አሸንፈዋል።

የዕለቱ የመጀመሪያ መርሐ ግብር ተከታታይ ድል እያስመዘገበ የሚገኘውን ባቱ ከተማን ከሽንፈት መመለስ ካቃተው አዲስ ከተማ ያገናኘ ነበር። በተደጋጋሚ ነጥብ ከመጣል በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሱት ባቱ ከተማዎች ተጋጣሚዎቻቸው ላይ በመጀመሪያ አጋማሽ ሙሉ የጨዋታ የበላይነት ወስደዋል።

ባቱ ከተማዎች በ4ኛው ደቂቃ ኳስን እየገፉ ወደፊት በሚሄዱበት ጊዜ የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ተከላካዮች ኳስን በእጃቸው ነክተው ፍፁም ቅጣት ምት አግንተዋል።ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ብርሃኑ አዳሙ አስቆጥሮ 1-0 መምራት ችለዋል። አዲስ ከተማ በአንፃሩ ካለባቸው ውጤት ማጣት ለመውጣት ሲሉ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውለዋል። ሆኖም ግን ጥሩ ሆኖ የዋለውን የባቱ ከተማን ተከላካይ መስመር አልፎ ግብ ማስቆጠር አቅቷቸዋል።

የጨዋታ ብልጫ የወሰዱት ባቱ ከተማዎች በ34ኛው ደቂቃ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ወንደወሰን በለጠ ከእስራኤል ሸጎሌ ጋር ባንድ ለአንድ ቅብብል ያገኘውን ኳስ ከግብ ክልል ውጪ ሆኖ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ዕረፍት 2-0 እየመሩ እንዲወጡ አስችሏል። ቀጣዩ አርባአምስት ብዙ የግብ ሙከራ ያላስመለከት ሲሆን ሁለቱም ቡድን ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩበት አጋማሽ ነበር። በዚህም በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ባቱ ከተማ ተጨማሪ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።

በማስከተል የተደረገው መርሃ ግብር የምድብ መሪውን አርባምንጭ ከተማን ከጋሞ ጨንቻ አገናኝቷል። የድንጉዛ ደርቢ ብሎ የሚጠሩት ይሄ ጨዋታ ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመልካች ያስመለከተ ነበር። የመጀመሪያ አጋማሽ በአርባምንጭ ከተማ መሪነት የተጠናቀቀ ሲሆን ጋሞ ጨንቻዎች ከደርቢያቸው በመጀመሪያ አጋማሽ ነጥብ ለመጋራት ሲጣጣሩ ተስተውለዋል።

ለአርባምንጭ ከተማ በ19ኛው ደቂቃ ግዙፉ አጥቂያቸው አህመድ ሁሴን በእርስ በእርስ ቅብብል የተገኘውን ግብ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪ እንዲሆኑ አስችሏል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ጋሞ ጨንቻዎች ብዙ ለግብ የተቃረበ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ጥሩ አጋጣሚዎችንም አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

አርባምንጭ ከተማዎችም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት ችለዋል። ሆኖም ግን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር የመጀመሪያ አጋማሽ 1-0 በአርባምንጭ ከተማ መሪነት ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

 

ከመልበሻ ክፍል መልስ ጋሞ ጨንቻዎች የአጨዋወት ስልታቸውን በመቀየር ኳስን ተቆጣጥረው ወደፊት ሲጫወቱ እና የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ነበር። ከብዙ ሙከራ በኋላ በ56ኛው ደቂቃ ላይ አምበላቸው ለገሰ ዳዊት ከአርባምንጭ ተከላካዮች ተነካክቶ የወጣውን ኳስ አክርሮ መትቶ አስቆጥሮ 1-1 አድርጓቸዋል።

አቻ ከሆኑ በኋላ ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቀሴ ለመመለከት ችለናል። ሁለቱም ቡድኖች የግብ ዕድል ለመፍጠር እንቅስቃሴ አድርገዋል። ሆኖም ግን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር እስከ 85ኛው ደቂቃ ድረስ በአቻ ውጤት ለመቀጠል ተገደዋል። ነገር ግን የተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉት አርባምንጭ ከተማዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ቀርቶ እያለ በ85ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ በፍጥነት በመድረስ አህመድ ሁሴን አስቆጥሮ ነጥብ ከመጋራት አውጥቶ የማሸነፍ ተስፋቸው እንዲለመልም አድርጓል።

ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በጫና የተጫወቱት አዞዎቹ በ88ኛው ደቂቃ በፍቅር ግዛቸው እና ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ መኮንን ተቀባብለው ፍቃዱ ኳስና መረብ አገናኝቶ የማሸነፊያ የግብ ልዩነታቸውን ማስፋት ሲችል ጨዋታውም 3-1 ተጠናቋል።

ቀን ስምንት ሰዓት ላይ የምድብ ተከታዩን ነጌሌ አርሲን ከካፋ ቡና ያገናኘ መርሃ ግብር በነጌሌዎች በላይነት ተጠናቋል።

በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ግብ ለማስቆጠር ከመሞከር ይልቅ የመከላከል ባህርይ ያሳዩበት አርባአምስት አስመልከተዋል። ቢሆንም ከምድቡ መሪ ነጥባቸው እንዳይርቅ ጨዋታውን ማሸነፍ ግድ የሆነባቸው ነጌሌዎች በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ሲያሳድሩ ተመልክተናል።

ካፋ ቡናዎች በአንፃራቸው ደረጃቸውን ለማሻሻል ነጥቡን ለማሳካት ግቦችን ለማስቆጠር የተጣጣሩበት የተሳካ አርባአምስት ማሳለፍ የቻሉ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ 0-0 ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብለው የገቡት ነጌሌዎች ፍፁም የጨዋታ በላይነት ወሰደው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። እንዲሁም በቁጥር በርከት ያለ ለግብ የተቃረበ ሙከራ ነጌሌ አርሲዎች አድርገዋል። ካፋ ቡናዎች ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ደካማ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

ለነጌሌ አርሲዎች የጥረታቸው ውጤት ፍሬ አፍርቶ በ50ኛው እና በ58ኛው ደቂቃዎች ግብ አስቆጥረው የጨዋታ ብልጫ መውሰዳቸውን ለተመለካች አረጋግጠዋል። በ50ኛው ደቂቃ የተከላካይ መስመር ተጫዋች የሆነው ያሬድ በልሁ ቦታውን ለቆ በመሄድ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ነጌሌዎች መሪ እንዲሆኑ አስችሏል።

ነጌሌዎቹ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ  በመነቃቃት ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ወደፊት ገፍተው ተጫውተዋል። በ58ኛው ደቂቃ የፊት መስመር ተጫዋቻቸው ታምራት ኢያሱ የካፋ ቡና ተከላካዮች የሰሩትን ክፍተት በብልጠት ተጠቅሞ ኳስና መረብ አገናኝቶ መሪነታቸውን አጠናክሯል።

ነጌሌ አርሲዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት የግብ ሙከራ ቢያድርጉም ሌላ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በአርሲ ነገሌ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የሳምንቱ ማሳረጊያ የሆነው ሳቢ የነበረው ጨዋታ ሸገር ከተማን ከቦዲቲ ከተማ አገናኝቶ በቦዲቱ ከተማ በላይነት ተጠናቋል።

ጥሩ ፉክክር በታየበት በ10 ሰዓቱ ጨዋታ ሁለቱም ቦድኖች ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመለካች ማሳየት ችለዋል። በምድቡ ጥሩ ተፎካከሪ በመሆን ሦስተኛ ደረጃ ይዘው የሚገኙት ሸገር ከተማዎች በአንደኛው አርባ አምስት በቦዲቱ ከተማዎች የግብ እና የኳስ ቁጥጥር ተወስዶባቸዋል።

ወደ ደረጃ ሰንጠረዥ ባይጠጉም በምድቡ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ኳስን ይዘው ከሚጫወቱ ቡድኖች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠሩት ቦዲቲ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር አድርገዋል። በ15ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ተስፋዬ ኳስን ይዞ ወደ ግብ ክልል በሚገባበት ሰዓት የሸገር ከተማው ተከላካይ ታምራት አየለ ጥፋት ፈፅሞበት ፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱንም ማሞ አየለ ወደ ግብነት ቀይሮ ቀዳሚ ግብ አስቆጥሯል።

የመጀመሪያ አጋማሽ ሊያልቅ አከባቢ ሸገር ከተማዎች አጋማሹን አቻ ሆነው ለመጨረስ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካላቸው ቀርተው 1-0 እየመሩ ወደ መልበሻ ለመግባት ተገደዋል። ከመልበሻ መልስ ተሽለው የገቡት ሸገሮች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የተቃራኒ ቡድን ግብ ለመድፈር ጥረዋል።

ጥረታቸው ተሳክቶ በ63ኛው ደቂቃ ያገኙትን ቅጣት ምት ዘነበ ከድር ወደ ግብ ያሻማትን ኳስ ግዙፉ ተከላካይ ሲሳይ ጥበቡ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር አቻ እንዲሆኑ አስችሏቸው ነበር። የአቻነት ግብ ከተቆጠረች በኋላ የጨዋታው ውበት የሆኑ ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ሁለቱም ቡድኖች በማድረግ ጨዋታው በይበልጥ ሳቢ እና ማራኪ እንዲሆን አድርገዋል።

1ለ1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ወደመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ድረስ መቀጥል ችሎ ነበር። ሆኖም ግን ከብዙ ሙከራዎች በኋላ በ83ኛው ደቂቃ ከሙሉቀን ተስፋዬ የተሻገረለትን ኳስ የመጀመሪያ ግብ አስቆጣሪው ማሞ አየለ አግኝቶ ኳስና መረብ አገናኝቶ ቦዲቲ ከተማዎች የማሸነፍ ተስፋቸውን እንዲጎናጸፉ አድርጓል። ከዚህም በኋላ ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 2-1 በሆነ የቦዲቲ ከተማ የላይነት ተቋጭቷል።