የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-2 ሲዳማ ቡና

“ከወትሮው በተለየ በከፍተኛ ሁኔታ የማጥቃት ጫና ነበረን” አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው

“ውጤቱ ጨዋታውን አይገልጸውም” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው

ሲዳማ ቡና በአዲሱ አሰልጣኙ ስር ሁለተኛ ድሉን በባህር ዳር ከተማ ላይ 2ለ0 በማሸነፍ ካስመዘገበበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቃለ ምልልስን አድርገዋል።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው ለእኛ በጣም ጥሩ ነበር ፣ ምክንያቱም ከወትሮው በተለየ በከፍተኛ ሁኔታ የማጥቃት ጫና ነበረን ፣ ከዛም አልፎ የተቆጠሩትም ግቦች ለዛ ማሳያ ናቸው። ጨዋታውን ታክቲካሊም ተቆጣጥረነዋል። ስለዚህ በጣም ጥሩ ነው ብሎ ማለፍ ይቻላል።”

ጨዋታውን መቆጣጠሩ እንዳለ ሆኖ ያሬድ ባዬ በቀይ መውጣቱ ታክቲኩ ላይ ጠቅሟል ማለት ስለመቻሉ…

“ብዙ ጊዜ በቀይ ከአንድ ቡድን ሲወጣ ተጋጣሚ ቡድን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ነቅሎ ነው የሚያጠቃው በዛ ላይ ደግሞ በግብ እየተመራ እንደገና ደግሞ በቀይ ሲወጣበት ያለው አማራጭ ማጥቃትን ብቻ ነው የሚያምነው ፣ በእኛ በኩል ደግሞ ያንን አማራጭ አይተህ ክፍት ነው ብለህ ገልበህ ወደፊት ዝም ብሎ መሄድ አስፈላጊ አይደለም ፣ ስለዚህ ጥንቃቄው ሳይዘነጋ ነገር ግን እነርሱ በሚፈጥሩት ክፍተት ማጥቃት ላይ ነበር ትኩረት አድርገን የነበረው እንደውም በሁለተኛው አጋማሽ ትንሽ የእኛ ተጫዋቾች ያቺን ለማስጠበቅ ወደኋላ አፈግፍገው ተጫውተው ነበር ፣ ምናልባት እኛም ወደፊት ተጭነው እንዲጫወቱ ስንጨቀጭቃቸው ነበር የዛም ምክንያት ነው ሁለተኛ ጎል ያስቆጠርነው ፣ ስለዚህ ታክቲካሊም ምንም አያጠያይቅም በቀይ መውጣቱ ለእኛ ሌላ ነገር እንድናስብ እንድንፈጥር ያስገድደናል።”

ቡድኑን ከያዙ በኋላ በሦስት ጨዋታው ሰባት ነጥቦችን ስለማግኘታቸው እና ቡድኑ ውስጥ ፈጠርኩት የሚሉት ነገር…

“በቡድኑ ውስጥ ተፈጥሯል የሚባለው ምንድነው ፣ አንደኛ ሲዳማ ቡና ትልቅ ክለብ ነው። በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ክለቦች በጣም ትልቅም የሚባል ቡድን ነው በዛው ልክ ደግሞ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሊሆኑ የሚችሉ ተጫዋቾችም በአብዛኛው አከማችቷል ፣ ያ ማለት መጠነኛ የሆነ ክፍተት የለበትም ማለት አይደለም ፣ እርሱ ሳይዘነጋ እነዚህን ተጫዋቾች የሚመጥን ፣ ክለቡን የሚመጥን ውጤት ግን እየመጣ አልነበረም ፣ ደጋፊውንም የሚመጥን ውጤት እየመጣ አልነበረም ፣ ስለዚህ ይሄን ማስተካከል ነው የነበረው እቅዳችን ፣ አንደኛ መስራት እንዳለብን ነው የተማመነው ፣ የነበሩ መልካም ነገሮች እንዳሉ ሆነው ግን መጠነኛ ወይም ከመጠን ያለፈ ትንሽ የፊትነስ ችግሮች እንዳሉ ቡድኑ ያሳይ ነበር እዛ ላይ ሰርተናል። ከመስራታችን በፊት ግን ሁሉም ተጫዋች እነርሱን የሚመጥን ክለቡን ወይም ደጋፊን የሚመጥን ክለብ ማሳየት እንዳለብን ተማምነናል። ከምንም ነገር የሚቀድመው ይሄ ነው ስለዚህ በዛ መነሻነት ጥሩ የማሸነፍ ፣ የመስራት ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርገናል።  የዛም ውጤት ነው በየጨዋታው የበለጠ እየተሻሻሉ እያማሩ የመጡት እና ትልቁ ስራችን እርሱ ነበር የነበረው።”

ስለ ክለቡ የመከላከል ጥንካሬ…

“ከጅምሩም የሲዳማ የመከላከል አቅማቸው ትልቅ ነው ፣ ግን እኛ ያደረግነው ምንድነው ያንን ፎርም የማስያዝ ፣ የበለጠ የማደራጀት ስራን ነው የሰራነው እንጂ የመከላከል ሂደቱ ላይ ብዙም ክፍተት አልነበረውም ፣ አስቀድሞም ግን አጠናክሮ መሄድ ግድ ስለሆነ ፎርም እንዲኖረው አድርገናል።”

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ሆነው ስለተሸነፉበት ጨዋታ…

“ጨዋታው ጥሩ ነው ፣ ተጫዋቾቻችን ጥሩ እየተጫወቱ በነበረበት ወቅት ነው ከቅጣት ምት ጎል ያስተናገድነው እዛ ላይ ሰዎችን በአግባቡ ተቆጣጥረን መያዝ ይገባን ነበር። ያ ስህተት ተፈጥሯል ነገር ግን እንደ ነበረው የዕለቱ ጨዋታ ማሸነፍ የሚገባን ነበር ፣ ውጤቱ ጨዋታውን አይገልጸውም። ተጫዋቾቻችን በጣም ጥሩ ነበሩ ጥሩ የማጥቃት ሜንታሊቲን ይዘው ነበር የገቡትም ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር የነበረው ሆኖም ግን ጫናውን ፈጥረን ጎል ለማግባት በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ደግሞ አላስፈላጊ ቀይ ካርድ ያስተናገድንበት ሁኔታ ነው ያለው ፣ እንዲህ አይነት ነገር ይከሰታል ፣ ያሬድን ማጣታችን ግን በጣም ጎድቶናል በተለይ በሁለተኛው አርባ አምስት በዚያን ያህል ጫና በዚያን ያህል ብልጫ እየተጫወትን እንደሚታየው ጎዶሎ አይመስልም ነበር በሙሉ እነርሱ ጎል ጋር ነበር የምንደርሰው ፣ ያሬድ ኖሮ ቢሆን ደግሞ የተሻለ ይሆን ነበር ፣ ያሬድ በአሁኑ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ጨዋታ ይጎዳናል። ለያሬድ መውጣት ግን ሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ የልጆቻችን እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ነበረው ፣ የመጣደፍ ፣ የመዋከብ እንቅስቃሴ የፈጠረው ችግር ነው። እንደ አጠቃላይ ግን ዘጠና ደቂቃ ሙሉ የጨዋታውን ውጤት ለመቀየር የሄዱበት ርቀት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው ጎሉ ጨዋታውን አይገልጸውም።”

የሚታወቀው የባህርዳር የሽግግር አጨዋወት አለ ወይስ ተዳክሟል…

“እርሱ ላይ ነው እየሰራን ያለነው አሁን ትኩረትም ሰጥተን ለማስተካከል ጥረት እያደረግን ያለነው እርሱ ላይ ነው። ያጣነው ይሄንን እንቀስቃሴ ነው ፣ እንደ ቡድን የመጫወት ፣ እንደ ቡድን የመንቀሳቀስ በአጠቃላይ እንደ ምንታወቅበት የጨዋታ መንገድ ያለፉትን ሁለት ጨዋታ ላይ አላከናወንም። በዛሬው ጨዋታ ግን ያንን የመለስንበት ቶሎ ቶሎ ወደ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል የደረስንበት እና አደገኛ ሙከራዎችን ያደረግንበት እንቅስቃሴ ነበር የነበረው ፣ ስለዚህ መሻሻሎች እንዳሉ ያሳያል ፣ በቀጣይ ከዚህም በተሻለ ሁኔታ የምናውቀውን ባህርዳር ከተማን ይዘን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ። እንደ አጠቃላይ ግን ተጫዋቾቻችን ዛሬ ለነበራቸው ተጋድሎ ትልቅ ትልቅ አክብሮት ነው ያለኝ ፣ አንገት  የሚያስደፋ ውጤት ሳይሆን እጅግ እጅግ በጣም የሚያስደስት እንቅስቃሴ ያየንበት በዕርግጥ እግር ኳስ ውስጥ እንዲህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ የመጣውን መቀበል ነው።”