መረጃዎች | 43ኛ የጨዋታ ቀን

በአስራ አንደኛው የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚደረጉ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልክ ቀርበዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በተለያየ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙ ቡድኖችን ያገናኛል።

በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ የቻሉት የጦና ንቦቹ በአስራ ሰባት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻው ጨዋታ የሊጉ መሪ ንግድ ባንክ ላይ ከተቀዳጁት ጣፋጭ ድል በኋላ ከመሪው ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ስድስት ነጥቦች በማጥበብ ምን ያህል ጠንካራ ስብስብ እንዳላቸው አስመስክረዋል። ቡድኑ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ካሉ ሦስት ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሁለቱን ማሸነፍ ችሏል ፤ ይህም ከሰበሰበው ነጥብ በተጨማሪ የቡድኑን መሻሻል ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የጣና ንቦች ከዚህ ቀደም የግብ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች ነበሩባቸው ፤ አሁን ግን የማጥቃት አጨዋወታቸው መጠነኛ መሻሻል አሳይቷል። በሊጉ ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ካለው ንግድ ባንክ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የነበራቸው እንቅስቃሴቃም ማሳያ ነው። በጨዋታው አንድ ግብ ቢያስቆጥሩም በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ የነበራቸው የማጥቃት ብልጫ የመሻሻላቸው ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። የወጣቱ አጥቂ ቢንያም ፍቅሩ ጥሩ እንቅስቃሴም የማጥቃት አጨዋወቱን አጎልብቶታል።

ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት አስተናግደው በመጥፎ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ከፍ ብለው 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ኃይቆቹ ከመቻል ጋር ባደረጉት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ መጥፎ የሚባል እንቅስቃሴ ባያሳዩም ከሽንፈት አልዳኑም። በጨዋታው ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ባይሆንም በሁለቱም አጋማሾች ላይ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ብልጫ መውሰድ ችለው ነበር። አሰልጣኝ ዘርስዓይ ሙሉ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ በአማካይ 2.4 ግቦች ያስተናገደውና በቀላሉ ግቦች እያስተናገደ ያለው የተከላካይ መስመራቸው ላይ ለውጥ ማድረግ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ በተከላካይ መስመሩ ካለው ክፍተት በተጨማሪ ስል ያልሆነና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ የፊት መስመር ቢኖረውም የኋላ ክፍሉ ችግር ግን ቶሎ መፈታት ያለበት ክፍተት ነው።

የቡድን ዜናን በተመለከተ በወላይታ ድቻ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት ባዬ ገዛኸኝ እና መልካሙ ቦጋለ በተጨማሪ አብነት ደምሴ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ በእግድ ከሚገኘው ሙጂብ ቃሲም ውጭ ሙሉ ቡድኑ ለጨዋታው ዝግጁ ነው፤ በቅጣት ላይ የነበሩት መድሐኔ ብርሀኔ እና እዮብ ዓለማየሁም ከቅጣት ተመልሰዋል።

ተጋጣሚዎቹ በሊጉ እስካሁን 18 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 7 ጊዜ ሲያሸንፍ ሀዋሳ 5 አሸንፏል። በስድስት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው 40 ጎል ሲቆጠር እኩል ሃያ ጎሎች አስቆጥረዋል።

ጨዋታው በኢንርተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ የመሐል ዳኝነት ሲመራ፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አሸብር ታፈሠ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በተከታታይ ድል አልባ ጉዞ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኘውን ጨዋታ ምሽት 12:00 ላይ ይጀምራል።

በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት አስተናግደው ወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ስምንት ነጥቦች ሰብስበዋል። ሠራተኞቹ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ በፋሲል ከነማ ቢሸነፉም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርገው አንድ ለባዶ ለመሸነፍ ተገደዋል። ቡድኑ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዶ በውጤት ረገድ መጥፎ የሚባል ቁጥሮች ቢያስመዘግብም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን መሻሻሎች አሳይቷል። በሊጉ የመጨረሻ ሳምንታት በጠንካሮቹ ወላይታ ድቻና ፋሲል ከነማ ሽንፈት ባጋጠማቸው ጨዋታዎች ያሳዩት እንቅስቃሴም መጥፎ የሚባል አደለም፤ ሆኖም ከኳስ ቁጥጥር ባለፈ ግብ ማስቆጠር ላይ የላቸው ክፍተት መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ላይ አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የአፈፃፀም ችግሩ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ላይም የአጨራረስ ችግራቸው መሻሻል አለበት ብለው እንደሚያምኑ ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ማሳካት የቻሉት አዳማ ከተማዎች አስራ አራት ነጥቦች ሰብስበው በ9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አዳማዎች ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፉበት የስድስተኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም ፤ በሁለቱ ነጥብ ተጋርተው በተቀሩት ሁለት ደግሞ ሽንፈት አስተናግደዋል። ቡድኑ በማጥቃቱ በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መጥቷል፤ አሰልጣኝ ይታገሱ እንደለ በተጠቀሱት አራት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የቡድኑ ፊት መስመር ወደ ቀደመው ጥሩ ብቃቱ እንዲመለስ የማድረጉ ስራ ይጠብቀዋል። ቡድኑ በመቻል ከደረሰበት ሽንፈት በፊት ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ያንኑ ጥንካሬ ይዞ መዝለቅ አልቻለም። ከመጨረሻው የአቻ ውጤት በኋላ በሰጡት አስተያየት የአማካይ ክፍላቸው የፈጠራ ችግር እንደሌለበት የገለፁት አሰልጣኝ ይታገሱ በነገው ጨዋታ ላይ ለአማካይ ክፍሉ ይልቅ የፊት ጥምረታቸው ላይ ለውጥ አድርገው የሚገቡበት ዕድል የሰፋ ነው።

ተስፋዬ መላኩ ከአራት ጨዋታዎች ቅጣቱ የተመለሰላቸው ወልቂጤዎች ከጉዳትም ሆነ ቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብ ይዘው ለጨዋታው ይደርሳሉ። ለሀገሩ ወደ ዕረፍት አቅንቶ የነበረው ቻርልስ ሪባኑ መመለሱን ተከትሎ አዳማ ከተማዎች ለነገው ጨዋታ በሙሉ ስብስባቸው ተዘጋጅተው የሚቀርቡ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስድስት ጊዜያት ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ አራቱን ጨዋታዎች በተመሳሳይ 1-1 አቻ አጠናቀዋል። አዳማ 7፣ ወልቂጤ 6 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

በዚህ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ዓለማየሁ ለገሠ የዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሲመራ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ ረዳቶቹ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።