ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | የ13ኛ ሣምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

በምድብ “ሀ” 13ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ንብ እና ሃላባ ከተማ ድል ሲቀናቸው ነቀምቴ ከተማ እና ወልዲያ ነጥብ ተጋርተዋል።

ረፋድ 3:30 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ንብን ከጅማ አባጅፋር  አገናኝቶ በንብ አሸናፊነት ተጠናቋል።


ሦስት ግቦችን በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ጅማ አባ ጅፋር ተሽለው ተገኝተዋል። በአንፃሩ በንብ በኩል በጥብቅ መከላከል እና ጥንቃቄን በማስቀደም ሲጫወቱ ተስተውሏል። በ28ኛው ደቂቃ በጅማ አባጅፋር የተከላካይ ክፍል አለመግባባት ኳስ እግሩ ውስጥ የገባው የንብ ተጫዋች ሀብታሙ ኃይሌ ለልማደኛው ግብ አስቆጣሪ ናትናኤል ሰለሞን በማቀበል በቀላሉ በማስቆጠር ንብን መሪ ማድረግ ችለዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላም እንደመጀመሪያው አጨዋወት በጥንቃቄ በመጫወት የሚያገኙትን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ንብ ጥረት ሲያደርግ ጅማ አባ ጅፋር ግብ ለማስቆጠር የተቃራኒ የግብ ክልል ጥሶ ለማለፍ ሲቸገር ተስተውሏል። በ39ኛው ደቂቃ ንብ ወደራሱ ግብ አፈግፍጎ በሚጫወትበት ጊዜ የተገኘውን ኳስ ከጥልቀት ለፊት መስመር ተጫዋቹ ናትናኤል ሰለሞን የተሻገረውን ኳስ ለእዮብ ዳዊት አመቻችቶ በማቀበል እዮብ ዳዊት የንብን መሪነት ያጠናከረ ግብ አስቆጥሯል። የአጋማሹ መጠናቀቂያ በ45ኛው ደቂቃ በድጋሚ የንብ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ናትናኤል ሰለሞን በግል ጥረቱ በጥልቀት በመነሳት የሳሳውን የጅማ አባጅፋር የተከላካይ ክፍል በቀላሉ አልፎ ፍጹም ግብ ጠባቂው ሊመልሰው በማይችልበት ሁኔታ አስቆጥሮ አጋማሹን ንብ በሦስት ጎል ልዩነት እየመራ እንዲወጣ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባጅፋር የዘገየ ቢመስልም ተጨማሪ ግብ ላለማስተናገድ የተከላካይ ክፍሉን ለማሻሻል የተጫዋች ቅያሪ አድርገዋል። ንብ በተረጋጋ መንፈስ እና የጨዋታውን ፍጥነት በመቆጣጠር ብዙም ለዐይን ሳቢ እና በሙከራ ያልታጀበ አጋማሽ አስመልክተውናል። በ79ኛው ደቂቃ የጅማ አባጅፋሩ ፊልሞን ገ/ጻድቅ ከመስመር በመነሳት አደገኛ የግብ ዕድል ቢፈጥርም ወደ ግብ መቀየር ተስኖት ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ንብ 3-0 አሸንፏል።

ውጤቱን ተከትሎ ንብ አዲስ አበባ ከተማ እስከሚጫወት ነጥቡን በማሳደግ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

5:30 የጀመረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ነቀምቴ ከተማን ከወልዲያ አገናኝቶ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ነጥብ ተጋርተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም ለዐይን ሳቢ ያልሆነ እና  በግብ ሙከራ ያልታጀበ እና በሁለቱም ቡድኖች የተሻለ ጨዋታውን የማሸነፍ ፍላጎት ያልተመለከትንበት ሁኔታ ተስተውሏል። በሁለቱም ቡድኖች የተቆራረጠ እና ፍሰት የሌለው አጨዋወት ተጫውተዋል። ነቀምቴ ከተማ የተወሰኑ ከቡድኑ ጥሩ እና ቋሚ ተጫዋች ዕረፍት በመስጠት ያላሰለፈ ሲሆን ወልዲያ በመጠኑ ወደ ፊት ለመጫን ጥረት ቢያረጉም ግብ ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። በሁለቱም ቡድኖች ተቀይረው የገቡት ተጫዋቾት ቡድናቸው ለማነቃቃት ሲሞክሩ ተስተውሏል። ሆኖም በዚህም አጋማሽ ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳንመለከት ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

7:30 ላይ የዕለቱ ሦስተኛ መርሐግብር ሃላባ ከተማን ከኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ አገናኝቶ ሃላባ ከተማ ድል አድርጓል።


በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። ሃላባ ከተማ ኳስን በመያዝ እና መስርቶ በመሄድ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። በአንጻሩ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ኳስን ለተጋጣሚው በመልቀቅ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ሲጥር ታይቷል። በ23ኛው ደቂቃ ሃላባ ከተማ ከተቃራኒ ቡድን የማዕዘን ምት መምቻ አካባቢ ወደ ግብ ሰለሞን ያለው የመታውን ኳስ የኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ግብ ጠባቂ ደካማ ብቃት ተጨምሮበት ሊቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ጥብቅ እና ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወትን አስመልክተውናል። አጋማሹም በሃላባ ከተማ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛውን አጋማሽ ኮልፌ ቀራኒዮ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የሃላባ ከተማን የተከላካይ ክፍል ሰብረው ለመግባት ሲቸገሩ ታይቷል። ጨዋታውም በዚሁ ሁኔታ ቀጥሎ ምንም ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው በሃላባ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።