የአፍሪካ ዋንጫ | የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ በኢትዮጵያዊ አልቢትር ይመራል

ዛሬ ምሽት የሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ በኢትዮጵያዊው አልቢትር ባምላክ ተሰማ ዳኝነት ይመራል።

34ኛ የአፍሪካ ዋንጫ እጅግ ሞቅ ባለ ድባብ ያለፉትን ሦስት ሳምንታት በአይቮሪኮስት ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል። “የምን ጊዜውም ምርጡ የአፍሪካ ዋንጫ” የሚል ተቀፅላ የተሰጠው ውድድሩ ነገ ምሽት በአዘጋጇ አይቮሪኮስት እና ናይጄሪያ መካከል በሚደረግ የፍፃሜ ጨዋታ ይደመደማል። ከነገው የፍፃሜ ፍልሚያ በፊትም ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት 3ኛ ደረጃን ለመያዝ ደቡብ አፍሪካ እና ዲ አር ኮንጎ የደረጃ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ይህንን ጨዋታም ኢትዮጵያዊው አልቢትር ባምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት እንደሚመራው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ባምላክ ከሁለት ሞሮኳዊ ረዳቶቹ እንዲሁም ሱማሌያዊ አራተኛ ዳኛ ጋር በጋራ ጨዋታውን የሚያጋፍር ይሆናል።