የመጀመርያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ  ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

ክለቦችን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች…

ለአስራ አምስት የጨዋታ ሳምንታት የዘለቀው  የመጀመርያው ዙር ከስምንት ቀናት በፊት መጠናቀቁ ይታወሳል። ሶከር ኢትዮጵያም በመጀመርያው ዙር ሊነሱ ይገባቸዋል ያለቻቸውን ክለቦችን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎች እንደሚከተለው አሰናድታለች።

በርካታ ጨዋታዎች ያሸነፉ ክለቦች

በአንድ ነጥብ ተበላልጠው በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጡት መቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካከናወኗቸው 15 ጨዋታዎች 10 በማሸነፍ በአንደኛነት ተቀምጠዋል።

የሊጉ መሪ መቻል ማግኘት ከሚገባው አርባ አምስት ነጥብ ሰላሣ ሦስቱን በማሳከት ከፍተኛውን ነጥብ መሰብሰብ ችሏል፤ ቡድኑ በመጀመርያው ዙር ሦስት አቻ እና ሁለት ሽንፈት አስመዝግቦ አስራ ሁለት ነጥቦች ጥሏል። ተከታዩ ንግድ ባንክ በበኩሉ ከመሪው በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሰላሣ ሁለት ነጥቦች ሰብስቧል፤ ቡድኑ በመጀመርያው ዙር ሦስት ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል።

ጥቂት ሽንፈት ያስተናገዱ ክለቦች

ጥቂት ሽንፈቶች በማስተናገድ በቀዳሚነት የተቀመጡት ክለቦች ሦስት ናቸው። መሪው መቻል፣ አዳማ ከተማና ሀድያ ሆሳዕና በተመሳሳይ በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ሽንፈት ቀምሰዋል።

አዳማ ከተማዎች በተመሳሳይ ጥቂት ሽንፈቶች ባስተናገዱት መቻልና ሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ሲያስተናግዱ መቻል ደግሞ በሁለተኛ እና አስራ አራተኛ ሳምንት ላይ በባህርዳር ከተማና ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ደርሶበታል። ሀድያዎችም በመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት በመቻልና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ከፍተኛ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡ ክለቦች

በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀድያ ሆሳዕና በአስር ጨዋታዎች ላይ አቻ በመለያየት ከፍተኛውን የአቻ ውጤት ያስመዘገበ ክለብ ሆኗል። ካከናወኗቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ብቻ ማሸነፍ የቻሉት ሀድያዎች አሸንፈው ከሰበሰቡት ዘጠኝ ነጥብ ይልቅ በአቻ ውጤት ያጠራቀሙት የነጥብ መጠን ይልቃል። አዳማ ከተማዎች በስምንት ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ተካፍለው በመውጣት ይከተላሉ ፤ ኢትዮጵያ መድንና ሻሸመኔ ከተማም ስድስት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡ ክለቦች ናቸው።

በርካታ ጨዋታዎች የተሸነፉ ቡድኖች

አዲስ አዳጊዎቹ ሀምበርቾዎች ካከናወኗቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች በአስሩ ሽንፈት በማስተናገድ ይመራሉ። በታሪክ የመጀመርያው የፕሪሚየር ሊግ ድላቸውን ለማሳካት አስራ ሁለት ሳምንታት ለመጠበቅ የተገደዱት ሀምበርቾዎች ሲዳማ ቡናን ያሸነፉበት ጨዋታ የውድድር ዓመቱ ብቸኛው ድላቸው ነው። ቡድኑ አስር ሽንፈት፣ አንድ ድልና አራት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቦ በጨዋታ በአማካይ 0.4 በድምሩ 7 ነጥቦች በመሰብሰብ የመጀመርያውን ዙር አገባዷል። ወልቂጤ ከተማ ዘጠኝ ሽንፈት በማስተናገድ ይከተላል፤ ስምንት ሽንፈት ያስተናገደው ሻሸመኔ ከተማ ደግሞ በሦስተኛ ደረጃነት ተቀምጧል።

በርካታ ግቦች ያስቆጠሩ ክለቦች

ከፍተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረ ክለብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ከዓመታት በኋላ በተመለሰበት ሊግ ድንቅ አጀማመር ያደረገው ቡድኑ ባከናወናቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች ሀያ ሰባት ግቦች በማስቆጠር በቀዳሚነት ተቀምጧል። በርካታ የግብ ምንጭ ያላቸው ሐምራዊ ለባሾቹ በጨዋታ በአማካይ 1.8 ግቦች ማስቆጠር ችለዋል። ሀያ አምስት ግቦች ያስቆጠሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለተኛ ደረጃነት ሲቀመጡ መቻልና ኢትዮጵያ ቡና ሀያ አንድ ግቦች በማስቆጠር በሦስተኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል።

ጥቂት ግቦች ያስተናገዱ ክለቦች

በውድድር ዓመቱ ዘጠኝ ግቦች ብቻ ያስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች ጥቂት ግቦች በማስተናገድ ይመራሉ። ሀድያዎች ካከናወኗቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች በስምንቱ ግባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል። በግማሽ የውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 0.6 ግቦች ብቻ ያስተናገዱት ሀድያዎች መቻል ካስቆጠረባቸው ሦስት ግቦች ውጭ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ባለማስተናገድ አስደናቂ ቁጥር አስመዝግበዋል።

ረዥሙ ያለመሸነፍ ጉዞ

አስራ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ያላስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች ረዥም ያለመሸነፍ ጉዞ በማድረግ ይመራሉ። በሁለተኛው ሳምንት ላይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በራስ ላይ በተቆጠረች ግብ አማካኝነት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ለአስራ ሦስት ሳምንታት ሽንፈት ያላስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በተጠቀሱት ሳምንታት ሦስት ድሎችና አስር የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል።

በብዙ ጨዋታዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡ ክለቦች

259 ግቦች በተቆጠሩበት የመጀመርያው ዙር በርከት ባሉ ጨዋታዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡ ክለቦች ፋሲል ከነማና ሀድያ ሆሳዕና ናቸው። ካከናወኗቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች በስምንቱ ግባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡት ሁለቱ ክለቦች ጥቂት ግቦች በማስተናገድም ጥሩ ክብረ ወሰን አስመዝግበዋል። ሀድያ ሆሳዕና ዘጠኝ ግቦች ብቻ በማስተናገድ ሲመራ ፋሲል ከነማም አስራ ሦስት ግቦች ከተመዘገበበት ኢትዮጵያ ቡና በአንድ ግብ ልቆ በሦስተኛ ደረጃነት ተቀምጧል።

ረዥሙ የድል ጉዞ

ትልቅ የወጥነት ችግር በሚታይበት ሊግ ለተከታታይ ሳምንታት በድል የተጓዘው ክለብ በሰላሣ ሁለት ነጥቦች በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ከአራተኛ ሳምንት እስከ ዘጠነኛው ሳምንት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ተከታታይ ድሎች ያስመዘገበው ይህ ክለብ በስድስት ጨዋታዎች  አስራ አራት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ከንግድ ባንክ በመቀጠል በሁለተኛነት የተቀመጠው ክለብ ደግሞ የሊጉ መሪ መቻል ነው። ከአራተኛው እስከ ስምንተኛው ሳምንት ድረስ በተደረጉ ጨዋታዎች አምስት ተከታታይ ድሎች ያስመዘገበው ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። የወጥነት ችግር በታየበት የመጀመርያው ዙር ከሁለቱ  ክለቦች ውጭ ከተከታታይ ሦስት ጨዋታ በላይ ያሸነፈ ክለብ የለም።