ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ዴንማርክ ሊያመራ ነው

ወጣቱ የአዳማ ከተማ አጥቂ ለሙከራ ወደ ዴንማርኩ ክለብ ያቀናል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከሚታዩ ተስፈኛ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ከአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን መሠረቱን ያደረገው እና ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዋናውን ክለብ በማገልገል ላይ የሚገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ አንዱ ነው። ከአዳማ ከተማ አልፎ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ጭምር ጥሪ ደርሶት ሀገሩን በማገልገል ላይ የሚገኘው ተጫዋቹ ከሁለት ቀናቶች በኋላ ለሙከራ ወደ አውሮፓዊቷ ሀገር ዴንማርክ ለሙከራ ሊያመራ ስለመሆኑ ተሰምቷል።

በዴንማርኩ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ሊግ ላይ ከሚሳተፉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሆርሰንስ ክለብ ዮሴፍን ለሙከራ የጋበዘው ክለብ እንደሆነ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። በቀጣዮቹ ቀናት ለሙከራ ወደ ስፍራው የሚያቃናው ይህ ተጫዋች በክለቡ መልማዮች ረዘም ላሉ ጊዜያት ሲታይ እንደነበር የተሰማ ሲሆን ወጣቱ አጥቂ የተሰጠውን የሙከራ ጊዜ በብቃት የሚወጣ ከሆነ ከአዳማ ከተማ ጋር ተጫዋቹ ውል ስላለው ዳጎስ ያለ የዝውውር ገንዘብን ከዴንማርኩ ክለብ እንደሚያገኝም ጭምር አሰልጣኙ ገልፀዋል።

አጥቂው ዮሴፍ ታረቀኝ ከወራቶች በፊትም ወደ ግብፅ ለሙከራ አቅንቶ ከክፍያ አለመግባባት ጋር ቆይታው ሳይሳካ መመለሱ ይታወሳል።