ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በስተመጨረሻም ከድል ታርቋል

ወላይታ ድቻ ከዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት በኃላ ወደ ድል በተመለሱበት ጨዋታ ፈረሰኞቹን በመርታት ጥሩ ያልነበረውን የድሬዳዋ ቆይታቸውን በድል ፈፅመዋል።

ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ሶስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ዘላለም አባተ ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና አናጋው ባደግን አስወጥተው በምትካቸው ቢኒያም ፍቅሬ ፣ ፀጋዬ ብርሃኑ እና አንተነህ ጉግሳን ሲጠቀሙ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በተመሳሳይ ከባህር ዳር ከተማ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ተገኑ ተሾመን አስወጥተው በምትኩ አማኑኤል ኤሮቦን አስገብተዋል።

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ለነበረው ሙሉቀን መለሰ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ አጀማመር በነበረው ሲሆን በዚህም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመመልከት ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ለመጠበቅ የተገደድንበት ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በንፅፅር የተመለከትናቸው የተሻሉ ሙከራዎች በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል የተደረጉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከሳጥን ውጭ አማኑኤል ኤርቦ እና ዳዊት ተፈራ ያደረጓቸው ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

ቀስ በቀስ ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከፍ ባለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በተደጋጋሚ ወደ ድቻ ሳጥን በመድረስ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በ21ኛው ደቂቃም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር ፤ በ21ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ያሻማውን የማዕዘን ምት ኳስ አማኑኤል ኤርቦ በግንባር በመግጨት ግብ ቢሞክርም ኳሷ የግቡን ቋሚ ለትማ ወደ ውጭ ወጥታበታለች።

በብዙ መልኩ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለተኛ ሆነው የፈፀሙት ወላይታ ድቻዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን በ25ኛው ደቂቃ ማድረግ ሲችሉ በዚህም ብስራት በቀለ ከግራ ሳጥን ጠርዝ ያደረገውን ሙከራም ባህሩ ነጋሽ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል።

በአጋማሹ የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር የነበራቸው ፈረሰኞቹ በከፍተኛ ታታሪነት ሲከላከሉ የነበሩትን ወላይታ ድቻዎችን የመከላከል መዋቅር ለማስከፈት ከፍተኛ ፈተና ገጥሟቸው የተመለከትን ሲሆን በአጋማሹም ከአማኑኤል ኤርቦ እግር ወደ ሳጥን የተላከች ኳስ በወላይታ ድቻ ተጫዋቾች በእጅ ተነክቷል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ የነበራቸው ቢሆንም አልቢትር አሸብር ሰቦቃ ግን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል አድርገዋል።

በ36ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ በግሩም ሁኔታ ያሾለከለትን ኳስ ተጠቅሞ አማኑኤል ኤርቦ ከቢኒያም ገነቱ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያደረጋቸውን ሁለት ሙከራዎች በቢኒያም ገነቱ ጥረት እና በአማኑኤል ያለመረጋጋት ግብ ሳይሆኑ ቀሩ እንጂ የአጋማሹ አስቆጭ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር ፍፁም ቀዝቃዛ የነበረ ሲሆን በአጋማሹ ግን ወላይታ ድቻዎች ከመጀመሪያው በተሻለ የመልሶ ማጥቃት ፍላጎት ያሳዩበት ነበር።

ፈረሰኞቹ ከመጀመሪያው አንፃር ከኳስ ቁጥጥር በዘለለ በማጥቃቱ ረገድ ፍፁም ደካማ አጋማሽን ባሳለፉበት የሁለተኛ አጋማሽ ይህ ነው የሚባል ዕድል ለመፍጠር በጣሙን ተቸግረው ያስተዋልን ሲሆን በአንፃሩ ሁለት ተጫዋቾችን በጉዳት ምክንያት ቀይረው ለማስወጣት የተገደዱት ወላይታ ድቻዎች በተጫዋቾች ለውጥ ሆነ በአቀራረብ ለውጥ ማጥቃታቸው በሂደት ተሻሽሎ ተመልክተናል።

በ71ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ወላይታ ድቻዎች ያገኙትን አጋጣሚ ከቀኝ መስመር መነሻውን ባደረገ ማጥቃት አብነት ደምሴ ከሳጥን ውስጥ ወደ ጎል ያደረገው ሙከራ በበባህሩ ነጋሽ የተመለሰበት ሲሆን የተመለሰውን ኳስ ድቻዎች ወደ ግብ ቢሞክሩም ኳሷን ፍሬምፖንግ ሜንሱ በግሩም መከላከል ግብ ከመሆን ታድጓል።

በመጨረሻው 20 ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ስል የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በ79ኛው ደቂቃ መሪ መሆን ችለዋል ፤ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር የተፈጠረውን ዕድል ከቅጣት የተመለሰው ቢኒያም ፍቅሬ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን በመድረስ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ዘላለም አባተ ከሳጥን ጠርዝ በግሩም ሁኔታ አክርሮ በመምታት ቡድን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ በኃላ ይበልጥ ክፍት ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እጅግ አስደናቂ ብቃቱን ያሳየው ቢኒያም ፍቅሬ በመልሶ ማጥቃት የቡድኑን መሪነት ሊያሳድግ የሚችልበትን ኳስ በ83ኛው ደቂቃ ወደ ግብ ቢልክም ኳሷ በግቡ ቋሚ ተመልሳበታለች።

እጅግ የተነቃቃ አጨራረስ በነበረው ጨዋታ አማኑኤል ኤርቦ ለሁለተኛ ተከታታይ የጨዋታ ሳምንት በጭማሪ ደቂቃ ቡድኑን አቻ ሊያደርግ የሚችልበት አጋጣሚ ቢያገኝም ቢኒያም ገነቱ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ሲሆን በተቃራኒ ሳጥን ቢኒያም ፍቅሬ ያገኘውን ዕድል ለጥቂት ሳይጠቀምበት የቀረ ሲሆን በዚህም ጨዋታ በወላይታ ድቻዎች የበላይነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታ ጥሩ እንደነበር ገልፀው በመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታውን መጨረስ አለመቻላቸው ለሽንፈት እንደዳረጋቸው ገልፀው ለሽንፈቱም ኃላፊነት እንደሚወስዱ ገልፀዋል በአንፃሩ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በቢኒያም ፍቅሬ ቅጣት ተዳክሞ የነበረው ማጥቃታቸው ዛሬ ስለመሻሻሉ ያነሱ ሲሆን ጨዋታው በእቅዳቸው መልኩ የሄደ እንደነበር ገልፀዋል።