ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ነቀምቴ ከተማ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ድል ቀንቷቸዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 24ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ ሁለቱ ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀው ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተገባደዋል።

ቀዳሚ በነበረው በሦስት ሰዓቱ ጨዋታ ነቀምቴ ከተማ ንብን 3-1 ረቷል።

ተመጣጣኝ አጨዋወት ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ቢጠናቀቅም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር በርከት ያለ የግብ ሙከራ ያደረጉበት አጋማሽ ነበር። ነቀምቴ ከተማም በሙከራዎች የተሻሉ ነበሩ። ንብም ቀላል ማይባል አደገኛ ሙከራዎችን ቢያደርግም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ተገተገባዷል።

 

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብለው የገባው ነቀምቴ ከተማ ከዕረፍት እንደተመለሱ አደገኛ ሙከራ በማድረግ ግብ ማምረት ችሏል። ቡድኑ በ53ኛው ደቂቃ በቶሎዋቅ ተስፋዬ አማካኝነት የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥረዋል። በአንድ ለሁለት ቅብብል የተገኘውን ግብ ቶላዋቅ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ነቀምቴ ከተማ መሪ አደርጓል። በዚህ ብቻ ያላበቁት ነቀምቴዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ወደ ተቀራኒ ቡድን ሲሄዱ ተስተውለዋል። በዚህም በ68ኛው ደቂቃ ሌላኛውን ግብ አስቆጥረዋል። ከመሰመር የተሻገረለትን ግብ ኢብሳ በፍቃዱ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪነታቸውን ሁለት አድርገዋል። ንብ በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም የጨዋታ በላይነት ተወስዶባቸው ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉበትን አጋማሽ አሳልፈዋል። ይሄንን አጋጣሚ በሚገባ የተጠቀሙት ነቀምቴ ከተማዎች በ82ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ አክለዋል። ከመስመር በከሉ የተሻማውን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር መሪነታቸውን ወደሦስት አድርሷል። መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ ተጨማሪ በታየው ላይ የነቀምቴ ከተማ ተጫዋቾች በሰሩት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ናትናኤል ሰለሞን ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጨዋታው 3-1 በሆነ ውጤት ተገባዷል።

በሁለተኛው ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከስልጤ ወራቤ ተገናኝተው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለቱም በወራጅ ቀጠና ስጋት ውስጥ ያሉትን ቡድኖችን ባገናኘው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ስልጤ ወራቤ ፍፁም የጨዋታ በላይነት ያሳለፋበትን አርባአምስት ሲያሳየን ኮልፌ ቀራኒዮ ግብ ካስተናገዱ በኋላ ለመነቃቃት ጥረት ቢያደርጉም በኳስ ቅብብል ተበልጠው ተገኝተዋል። በዚህም በኳስ ቁጥጥር ጠንካራ የነበሩት ስልጤ ወራቤዎች ከተደጋጋሚ የግብ ሙከራ በኋላ ገና በስድስተኛው ደቂቃ ግብ አግኝተዋል። ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ሥዩም ደስታ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ጋር አገናኝቷል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ሌላ ግብ ሳያስመለከት 1-0 በሆነ በስልጤ ወራቤ መሪነት ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኮልፌ ቀራኒዮ ጠንከር ብለው በመግባት የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫና ሲያደርጉ ተስተውለዋል። እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ ተወስዶባቸው የነበረውን የጨዋታ በላይነት በማስመለስ በኳስ ቁጥጥር በልጠው መገኘት ችለዋል። ስልጤ ወራቤ በአንፃሩ ነጥቡን ለማስጠበቅ ወደኋላ ያፈገፈጉበትን አጋማሽ ሲያሳልፉ ለመመለከት ተችሏል። ይሄንን ውጤት ያልፈለጉት ኮልፌ ቀራኒዮች የአቻነት ግብ በ76ኛው ደቂቃ ከመረብ ጋር አገናኝተዋል። አዳነ ተካ በራሱ ጥረት ኳስን እየገፋ በመሄድ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መትቶ አቻ አድርጓቸዋል። በዚህም ጨዋታው በአቻ ውጤት ተገባዷል።

የቀን 8:00 ሰዓቱ ጨዋታ  ጅማ አባ ጅፋርን ከሀላባ ከተማ አገናኝቶ ያለግብ ተገባዷል።

ጥንቃቄ የተሞላበት በዚህ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር በመከልከል ሲጫወት የተስተዋለ ሲሆን ሀላባ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫውት ከባባድ ሙከራ ሲያደርግ ተስተውሏል። ጅማ አባ ጅፋርም ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶችን ይዞ ቢገባም በደካማ አጨራረስ ኳሶችን ሲያመክኑ ለመመለከት ተችሏል። በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የነበሩት ሀላባ ከተማዎች የሚያደርጉትን ከባባድ ሙከራ ግብ ጠባቂው ዮሐንስ በዛብህ ሲመልስባቸው ለመመለከት የተቻለ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽም ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሀላባ ከተማ በኳስ ቁጥጥር ፍፁም የጨዋታ በላይነት ቢወስድም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ውለዋል። ጅማ አባ ጅፋርም በመልሶ ማጥቃት የሚያገኙትን ኳስ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው ያለግብ ተገባዷል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡናይ ከኦሮሚያ ፖሊስ አገናኝቶ በኦሮሚያ ፖሊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሁለቱም አጋማሽ ኦርሚያ ፖሊስ ፍፁም የጨዋታ በላይነት በመውሰድ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ ለመመለከት ተችሏል ። ይርጋጨፌ ቡና በአንፃሩ ካለበት የውጤት ቀውስ ለመውጣት ቢያንስ በአቻ ውጤት ለመጨረስ በመከልከል ረገድ ጠንከራ መሆን ቢችሉም የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግብ አስተናግደዋል። በ43 ኛው ደቂቃ የመጨረሻ የሚባለውን የማዕዘን ምት ያገኙት ኦሮሚያ ፖሊሶች የማዕዘን ምቱ ተሻምቶ ምስጋናው ወልደ ዮሐንስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ዕረፍት 1-0 እየመሩ እንዲወጡ አድርጓቸዋል።

ከዕረፍት መልስ ይርጋጨፌ ቡና የጨዋታ ብልጫ ጋር አቻ ለመሆን ወደፊት ኳስ ይዞ በመግባት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርግም በደካማ አጨራረስ ኳሶችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ኦሮሚያ ፖሊስም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጠንከር ያለ ሙከራ አደርጓል። ሆኖም ግን መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት ተጠናቋል። በጭማሪ ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል የገቡት ኦሮሚያ ፖሊሶች በጭማሪ 2ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው በሽመልስ ቦጋለ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ አስቆጥረው ጨዋታው 2-0 እንዲጠናቀቅ ሆኗል።