“ውስጣችን ቁጭት ነበር ፣ አሁን ግን በጣም ደስተኛ ነኝ” አበበ ጥላሁን

ከእግር ኳስ ማህበረሰቡ ጋር የተዋወቀው በአርባምንጭ ከተማ ቆይታው ሲሆን በመቀጠል ግን ለሲዳማ ቡና ፣ መቻል እና ኢትዮጵያ ቡና በተከላካይ ስፍራ ላይ በመጫወት ረዘም ያለ ጊዜን አሳልፏል። በ2015 የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ወደ ቀድሞው ክለቡ አርባምንጭ ከተማ በመመለስ በቡድኑ ውስጥ በፕሪሚየር ሊጉ እየተጫወተ የነበረ ቢሆንም ክለቡ ያስመዘገበውን ውጤት ተንተርሶ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ለሁለተኛ ጊዜ ለመውረድ ተገዷል። ከቡድኑ ጋር አብሮ በመውረድ በከፍተኛ ሊጉ ምድብ “ለ” ቆይታን ያደረገው አምበሉ እና ተከላካዩ አበበ ጥላሁን ከአዞዎቹ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደጉ ስለ ተሰማው ስሜት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር አጭር ቆይታን አድርጓል።


የከፍተኛ ሊጉ ውድድር ምን ይመስል ነበር…

“ውድድሩ ጠንካራ ነው። በሁለት ዙር ነው የተደረገው ሀዋሳ ላይ በተለይ እጅግ ጠንካራ ነበር ፣ እዛም እያለን ነጥባችን ከተከታያችን አስፍተን መጥተናል። ወደ አዲስ አበባም ከመጣን በኋላ ጠንካራ ውድድርን እስከ መጨረሻው ማለት ይቻላል አድርገናል።”

ከክለቡ ጋር ወደ ታች ወርዶ ስለ መመለሱ…

“ከክለቡ ጋር ዓምና በፕሪሚየር ሊግ አብረን ነበርን እና ስሜቱ በጣም ከባድ ነበር ፣ በተለይ ስንወርድ በጣም አዝነን ፣ አልቅሰን ነበር ወደ ቤት የሄድነው አሁን ላይ ግን ያንን በአንድ ዓመት አሳክተናል። ውስጣችን ቁጭት ነበር አሁን ግን በጣም ደስተኛ ነኝ በአንድ ዓመት በመመለሳችን።”

በቀጣይ ክለቡ የመውረድ አደጋ እንዳይገጥመው መሠራት ስላለባቸው ጉዳዮች…

“ክለቡ ከዚህ በኋላ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ረጅም ጊዜ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቆይ በተለይ ጠንካራ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ፣ ከምንም በላይ አመራሩ ፣ አሰልጣኞችም ፣ ተጫዋቹም ትልቅ የቤት ሥራ ነው የሚጠብቀን ጠንክሮ መሥራት እና ራስን ማዘጋጀት ከአሁኑ ያስፈልጋል። በመጨረሻም ቤተሰቤንም ፣ ደጋፊዎቻችንንም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።”