ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አርባምንጭ ከተማ ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፎርፌ አግኝቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት በሁለተኛ ቀን ውሎ አርባምንጭ ከተማ ሲያሸንፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፎርፌ ሦስት ነጥብ አግኝቷል።

ረፋድ ላይ የተደረገው የአርባምንጭ እና ልደታ ክፍለ ከተማ ጨዋታ በአርባምንጭ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጨዋታው በጥቅሉ የልደታ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና የአርባምንጭ ውጤታማ ማጥቃት የታየበት ሲሆን 23ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል የተላከውን ኳስ ድንቅነሽ በቀለ አስቆጥራ ቡድኗን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።

ልደታዎች የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ጠንካራውን የአርባምንጭ ተከላካይ ማስከፈት ሳይችሉ አጋማሹ ተገባዷል።

ከእረፍት መልስ አርባምንጮች በቶሎ መሪነታቸውን ያሰፉበት ጎል አስቆጥረዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ክልላቸው የተሻገረውን ኳስ ሰርካለም ባሳ አግኝታ ከሳጥን ውጪ በመምታት ሁለተኛውን ጎል ማስቆጠር ችላለች።

ከጎሉ በኋላ ልደታ ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የአዞዎቹ የኋላ ክፍል ላይ ስጋት መደቀን ሳይችሉ ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሌላኛው የዛሬ መርሃግብር ከቀትር በኃላ 10 ሰዓት ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ይርጋ ጨፌ ቡና መካከል ሊደረግ የነበረው ጨዋታ ይርጋጨፌዎች ባለመገኘታቸው ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለ30 ደቂቃዎች ያክል በመጠበቅ በፎርፌ 3 ነጥብ እና 3 ግብ አግኝተው ከሜዳ ወጥተዋል።