ሪፖርት | ወላይታ ድቻዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል

የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በነበረው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች ከመመራት ተነስተው ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 በመርታት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።

ወላይታ ድቻዎች በ26ኛ ሳምንት ከተጠቀሙት የመጀመሪያ 11 ምርጫቸው ሦስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም አንተነህ ጉግሳ ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ቢኒያም ፍቅሬን አስወጥተው በምትካቸው ፍፁም ከበደ ፣ ናታን ጋሻው እና ኢዮብ ተስፋዬን በማስገባት ሲጀምሩ በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በኩል ደግሞ በመጨረሻ ጨዋታቸው ከተጠቀሙበት ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ግብ ጠባቂ ላይ ያሬድ በቀለን አስወጥተው በታፔ አልዛየር ብቻ ተክተው ወደ ዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

9 ሰዓት ሲል ጅማሮውን ባደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች እጅግ ፈጣን አጀማመርን ለማድረግ ጥረት ያደረጉበት ነበር በዚህም በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጨዋታውን በብዙ መመዘኛዎች ሁለተኛ ሆነው ለመጀመር የተገደዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግን ሳይጠበቁ በጨዋታው መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ፤ በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የደረሱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሳሙኤል ዮሀንስ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ ተመስገን ብርሃኑ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ እጅግ ተቀዛቅዞ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በወላይታ ድቻዎች በኩል በ25ኛው ደቂቃ ብስራት በቀለ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ናታን ጋሻው ከሳጥን ውስጥ በግንባሩ ሸርፎ የሞከራት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት አጋጣሚ እንዲሁም በሀዲያ ሆሳዕና በኩል በ40ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቲሳ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የሞከራት እና ለጥቂቅ በግቡ ቋሚ በኩል ወደ ውጭ ከወጣችበት አጋጣሚ ውጭ ተጠቃሽ የግብ ሙከራዎችን ሳንመለከት አጋማሹ በሀዲያዎች የ1-0 መሪነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ አውንታዊ አጀማመርን ማድረግ የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ገና ከጅምሩ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በ54ኛው ደቂቃም የአቻነቷን ግብ ማግኘት ችለዋል።ግዙፉ አማካይ አብነት ደምሴ ከቀኝ መስመር መነሻውን ባደረገ የማጥቃት ሂደት ብስራት በቀለ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሳጥን ጠርዝ ላይ የነበረው አብነት ደምሴ እርጋታ በተሞላበት መንገድ ቡድኑን ወደ አቻነት የመለሰች ግብን ማስቆጠር ችሏል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች ምላሽ ለመስጠት በተወሰነ መልኩ ከግቧ መቆጠር በኃላ ፍንጭ ቢሰጡም ይህ ጥረታቸው ብዙም መዝለቅ አልቻለም።እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽ ከፍ ባለ የማሸነፍ ፍላጎት መጫወታቸውን የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻዎች 15 ደቂቃዎች የማሸነፊያዋን ግብ ፍለጋ ይበልጥ ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉ ሲሆን በ79ኛው ደቂቃ ላይም ወደ ቀኝ ካደላ ስፍራ የተሻማን የቅጣት ምት ኳስ ናታን ጋሻው በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ሲችል በ83ኛው ደቂቃ ግን የሚገባቸውን የማሸነፊያ ግብ ማግኘት ችለዋል።

በጥሩ ሂደት የሀዲያ ሆሳዕና ሳጥን የደረሰውን ኳስ ናታን ጋሻው አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ የሀዲያው ግብ ጠባቂ ኳሷን ቢመልስም በቅርብ ርቀት የነበረው ብሩክ ማርቆስ ኳሷን ለማውጣት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ኳሷ ከመረብ ጋር መዋሀዷን ተከትሎ ጨዋታው በወላይታ ድቻዎች የ2-1 የበላይነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንደነበር ገልፀው በሁለተኛው አጋማሽ በመከላከል ረገድ ወርደው መቅረባቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው የገለፁ ሲሆን ግብ ጠባቂያቸው ታፔ አልዛየር በጨዋታው ያሳየው ብቃት ፍፁም ደካማም እንደነበር እንዲሁ ገልፀዋል በአንፃሩ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ከዕረፍት መልስ ያደረጓቸው ለውጦች ውጤት እንዳስገኘላቸው ገልፀው ቡድናቸው ለነገ የሚታይ ተስፋ እንዳለውም አያይዘው ገልፀዋል።