ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን 7ኛ ተከታታይ ድሉን አሳክቷል

በ27ኛ ሳምንት የማሳረጊያ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድን በሁለቱ አጋማሾች የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በተገኙ ግቦች ሰባተኛ ተከታታይ ድላቸውን ሻሸመኔ ከተማ ላይ አስመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ መድኖች አዳማ ከተማን ከረቱበት የመጀመሪያ 11 ምርጫ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ተከላካይ መስመር ላይ ሰዒድ ሀሰንን በርናንድ ኦቼንግ ብቻ ሲተኩ በአንፃሩ በሻሸመኔ ከተማዎች በኩል እንደ ኢትዮጵያ መድን ሁሉ ከመቻል ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ ኬን ሰይድን በአቤል ማሞ ተክተው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

እምብዛም በፉክክር የተሞላ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ መድኖች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የያዙበት እንዲሁም ሻሸመኔ ከተማዎች በቀጥተኛ ኳሶች እና ጫና በማሳደር በሚነጠቁ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር የሞከሩበት ነበር ፤ ነገርግን ሁለቱም ቡድኖች ለመተግበር በፈለጉት የጨዋታ ዕቅድ ውስጥ በማጥቂያው ሲሶ የነበራቸው ሂደት አመርቂ አልነበረም።

ኢትዮጵያ መድኖች በ2ኛው ደቂቃ አለን ካይዋ ከተከላካይ ጀርባ ሚሊዮን ሰለሞን በጣለለት ኳስ ከአቤል ማሞ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም አለን ኳሱን በቀላሉ መጠቀም ሲገባው ዘግይቶ ወደ ግብ ያደረጋት እና አሸብር ውሮ የመለሰበት ኳስ እንዲሁም በሻሸመኔ ከተማዎች በኩል በ37ኛው ደቂቃ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ ያሾለከለትን ኳስ ተጠቅሞ ሁዛፍ ዓሊ አቡበከር ኑራን አልፎ ያደረገውን ሙከራ በርናንድ ኦቼንግ ግብ ከመሆን ያዳነበት ሙከራ የአጋማሹ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ነገርግን የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ የሰከንዶች ዕድሜ ሲቀር የኢትዮጵያ መድኑ አብዱልከሪም መሀመድ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ ምንተስኖት ከበደ በግንባሩ ወደ ውጭ ለማውጣት አልሞ የሸረፋት ኳስ ወደ ግብነት ተቀይራ አጋማሹ በኢትዮጵያ መድኖች 1-0 የበላይነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በብሩክ ሙሉጌታ ምትክ መሀመድ አበራን በማስገባት የጀመሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድናቸው በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱን የመስመር ተከላካዮቻቸውን በሚዛናዊነት ወደ ውስጥ በማስገባት ይበልጥ የመሀል ሜዳ ቁጥጥራቸውን በማሳደግ ቶሎ ቶሎ ወደፊት ለመድረስ ሙከራ አድርገዋል።

ነገርግን በሂደት ሻሸመኔ ከተማዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ በመቀልበስ ይበልጥ ወደፊት ገፍተው መጫወት የቻሉ ሲሆን ሁዛፍ ዓሊ እና እዮብ ገ/ማርያምን በመጠቀም በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ መድን ሳጥን መድረስ ቢችሉም የኢትዮጵያ መድን ተከላካዮች ጊዜያቸውን የጠበቁ የኳስ ማቋረጦች ሻሸመኔን ከምኞታቸው እንዳይገናኙ ከልክሏቸዋል።

የሻሸመኔ ከተማዎች አንፃራዊ የበላይነት በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በ92ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ስንታየሁ መንግሦቱ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያደረገውን ግሩም ሙከራ አቡበከር ኑራ በግሩም ቅልጥፍና ሲያድንበት የተመለሰችው ኳስ በተቃራኒ አቅጣጫ ከደቂቃዎች በፊት ወደ ሜዳ የገባው አብዲሳ ጀማል በግል ጥረቱ በማስቆጠር ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን የ2-0 የበላይነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔ ከተማ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የነበራቸው እንቅስቃሴ ጥሩ እንደነበር ገልፀው በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የጥራት ልዩነት ውጤቱን እንደወሰነው አንስተዋል ፤ አክለውም በወራጅ ቀጠና ከሚፎካሯቸው ቡድኖች አንፃር የተሻለ ነገር ያላቸው ቢመስሉም ከጨዋታዎች ውጤት ይዘው እየወጡ አለመሆናቸው አሳሳቢ መሆን ገልፀዋል በአንፃሩ የአሸናፊው የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው ደካማ እንደነበር አንስተው የአሸናፊነት ስሜቱን ማስቀጠሉ በራሱ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ገልፀዋል።አክለውም ሊጉ መቋረጡ በራሱ የተወሰነ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸውም አልሸሸጉም።