መረጃዎች | 111ኛ የጨዋታ ቀን

28ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ነገ ሲጀምር ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ወሳኝ ሚና ያላቸውን ሁለት ጨዋታዎች ያስተናግዳል ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ላለመውረድ እየታገሉ የሚገኙትን ሻሸመኔ ከተማዎችን በሰንጠረዡ አጋማሽ ከሚገኙት ፋሲል ከነማዎች ጋር ያገናኛል።

በአሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ የሚመሩት ሻሸመኔ ከተማዎች የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኃላ በሚታይ መልኩ ሜዳ ላይ በእንቅስቃሴ መሻሻል ቢያሳዩም እንቅስቃሴያቸውን በውጤት ማጀብ አለመቻላቸውን ተከትሎ አሁንም በ14 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ጨዋታዎችን እጅግ በተሻለ ፍላጎት የሚጀምሩር ሻሸመኔ ከተማዎች በብልጫ በጀመሩባቸው ጨዋታዎች ሳይጠበቁ በሚያስተናግዷቸው ግቦች ጨዋታዎች ከእጃቸው ሲወጡ እያስተዋልን እንገኛለን ፤ በሁዛፍ ዓሊ እና እዮብ ገ/ማርያም የግል ብቃት ላይ የተንጠለጠለው የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ ዕድሎችን ወደ ግብነት ለመቀየር ተቸገረ እንጂ ቡድኑ እንደ ሰሞነኛ ብቃቱ በዚህ ደረጃ ላይ ባልተገኘ ነበር።

በሊጉ ለመቆየት ነገ ከፋሲል ከነማ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ጨምሮ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀምበሪቾ የሚገጥሙ ሲሆን በሊጉ ለመቆየት ከራሳቸው ውጤት ባለፈ የወልቂጤ ከተማን ነጥብ መጣል የሚጠብቁት ሻሸመኔዎች ከእነዚህ ከባድ ከሚመስሉ መርሐግብሮች ነጥቦችን አሳክተው በሊጉ ይቆዩ ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን እንደ አዲስ እየተገነባ የሚገኘው ስብስብ አሁን ላይ በ40 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን በመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1-0 ሽንፈትን አስተናግደዋል።

እንደ ቡድን በተጠበቁበት ደረጃ ለመገኘት የተቸገሩት ዐፄዎቹ በሰንጠረዡ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ ዕድል ያላቸው ሲሆን በቀሪዎቹ ሁለት የሊግ መርሐግብሮች ከወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጨዋታ የሚጠብቃቸው ሲሆን በሰንጠረዡ የተሻለ ስፍራን ይዘው ለማጠናቀቅ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በፋሲል ከነማ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል በተጨማሪ ኢዮብ ማቲያስ ፣ ይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ ይሁን እንዳሻው እና አምሳሉ ጥላሁን በነገው የፋሲል ስብስብ ውስጥ አይኖሩም። በሻሸመኔ በኩል ገዛኸኝ ደሳለኝ ከጉዳት ሲመለስ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ በጉዳት አይሰለፍም።

በሊጉ ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ዐፄዎቹ በድምሩ አራት ግቦችን አስቆጥረው ሁለቱንም መርታት ችለዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የምሽቱ መርሐግብር በመጨረሻ የሊግ መርሐግብራቸው በድምሩ ዘጠኝ ግቦች አስተናገደው የተሸነፉትን ሁለቱን ቡድኖች ያገናኛል።

በመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት በደጋፊዎቻቸው ፊት እጅግ አስደንጋጭ የሆነን የ5-0 ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዋሳ ከተማዎች ከዚህ ሽንፈት ለማገገም እና በባለፈው ጨዋታ ሽንፈት ያዘነውን ደጋፊ ለመካስ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።

እንደ ቡድን ወጥነት ያለው ውጤት ለማስመዝገብ ተቸግረው የውድድር ዘመኑን ለማጠናቀቅ የተቃረቡት ሀዋሳ ከተማዎች አሁን ላይ በ36 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ የነገውን ጨዋታ ጨምሮ ባህር ዳር ከተማን እና ወላይታ ድቻን የሚገጥሙ ይሆናል።

በአንፃሩ በሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ወልቂጤ ከተማዎች በእነዚህ ጨዋታዎች በድምሩ አስራ ስምንት ግቦችን ሲያስተናግዱ በአንፃሩ ሶስት ግቦችን ብቻ አስቆጥረዋል ፤ ካስቆጠሯቸው ግቦች ማነስ ባለፈ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ያለማስቆጠራቸው ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነው።

አሁን ላይ በ16 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላዬ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች በሊጉ የመቆየት ዕጣ ፈንታቸውን በእጃቸው ይገኛል ፤ ነገ ከሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ ጨምሮ በቀሪዎቹ መርሐግብሮች ሀምበሪቾ እና አዳማ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል።

ሀዋሳ ከተማዎች ከጉዳትም ሆነ ቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስባቸው ይዘው ሲቀርቡ በቅጣት ምክንያት ከመጨረሻው ጨዋታ ውጭ የነበረው ተከላካዩ ፀጋአብ ዮሐንስም ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። በወልቂጤ በኩል ክለቡ ላይ ቅሬታ ያለባቸው ዘጠኙም ተጫዋቾች ክለቡን ቢቀላቀሉም የመሰለፋቸው ነገር ነገ በሚያገኙት ጥቅማጥቅም ይወሰናል ተብሏል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 7 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ በአራት ድል ቀዳሚ ሲሆን ወልቂጤ አንድ አሸንፎ ሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል። ሀዋሳ ከተማ 10፤ ወልቂጤ ከተማ 7 ግቦች አስቆጥረዋል።