የክለቦች የዝውውር እንቅስቃሴ – ሲዳማ ቡና


በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾችን በሌሎች ክለቦች የተነጠቀው ሲዳማ ቡና በሌሎች ተጫዋቾች ለመተካት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከወዲሁም ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት እየደረሰ ይገኛል፡፡

ለመፈረም የተስማሙ

ፈቱዲን ጀማል

የወላይታ ድቻው ሁለገብ ተከላካይ ፈቱዲን ጀማል ከሀላባ ድቻን ከተቀላቀለ ወዲህ ባለፉት ሁለት አመታት መሻሻል ያሳየ ተጫዋች ሲሆን ሲዳማን ለመቀላቀል ከተስማሙ ተጫዋቾች ቀዳሚው ሆኗል፡፡ ወደ ድሬዳዋ ያመራው ሰንደይ ሙቱኩን ክፍተት ይደፍናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ወንድማማቾች . . .

የገዛኸኝ ወንድማማቾች በሲዳማ ቡና መገናኘታቸው እርግጥ ሆኗል፡፡ በመከላከያ ከጉዳት ጋር እየታገለ ያለፉትን 6 ወራት መልካም እንቅስቃሴ ያሳየው ባዬ ገዛኸኝ በከፍተኛ ገነዘብ ወደ ሲዳማ ቡና ሲቀላቀል በደቡብ ፖሊስ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት ያሳለፈው ሐብታሙ ገዛኸኝ የታላቅ ወንድሙን ፈለግ ተከትሎ ማረፍያውን ሲዳማ አድርጓል፡፡

አምሐ በለጠ

አማካዩ አምሐ በለጠ ያለፈውን የውድድር ዘመን በድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሳለፈ ሲሆን ከ6 ወራት የድሬዳዋ ቆይታ በኋላ ወደ ሲዳማ ቡና አምርቷል፡፡

ከወጣት ቡድን

ክለቡ ከወጣት ቡድኑ 5 ተጫዋች እንደሚያሳድግ ያስታወቀ ሲሆን በቅርቡ ያደጉት ተጫዋቾች ይታወቃሉ ተብሏል፡፡

ከጋና …

በዝውውር መስኮቱ የተከላካይ መስመሩ በእጅጉ የሳሳው ሲዳማ ቡና ክፍተቱን ለመሙላት 3 ተጫዋቾች ከጋና ማስመጣቱ ታውቋል፡፡ ሐምሌ 25 የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሲከፈትም በይፋ ይፈርማሉ ተብሏል፡፡ በግራ ተከላካይ እና አማካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው አብዱላጢፍ መሐመድ ፣ የተከላካይ አማካዩ አሺያ ኬኔዲ እንዲሁም የመሀል ተከላካዩ ሚካኤል አናን ለሲዳማ የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የ27 አመቱ አብዱልለጢፍ በጋቦኑ ሲፍ ሞናና ፣ በፊንላንዱ ኤፍ ኤስ ኢልቬስ እና በዛምቢያው ሉሳካ ዳይናሞስ በመጫወት ልምድ ያካበተ ተጫዋች ነው፡፡ የ23 አመቱ አሺያ ኬኔዲ በ2013 ከ20 አመት በታች አለም ዋንጫ ላይ 3ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው የጋና ከ20 አመት በታች ቡድን አባል የነበረ ሲሆን በኖርዌዩ ብራን ፣ በሱዳኑ አል ሂላል እና በሊቢያው ትሪፖሊ ኤስ ሲ ክለቦች ተጫውቷል፡፡ የ32 አመቱ ሚካኤል አናን የእግርኳስ ህይወቱን አመዛኝ ክፍለ ጊዜ በጋና ያሳለፈ ተጫዋች ነው፡፡

ውላቸውን ያደሱ ተጫዋቾች

ሁለተኛ ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ ለተጨማሪ ሁለት አመታት ውሉን ሲያድስ ናይጄርያዊው አጥቂ ላኪ ሰኒ በሪለዱም ሌላው ለሁለት አመታት ውሉን ያራዘመ አጥቂ ነው፡፡ መሉአለም መስፍን እና ለአለም ብርሀኑ በክለቡ ያላቸው ቆይታ ያልተረጋገጠ ሲሆን ከብሔራዊ ቡድን መልስ ቁርጣቸው ይለያል ተብሏል፡፡

ስማቸው ከሲዳማ ጋር የተያያዙ ተጫዋቾች

በርካታ ተጫዋቾች ከሲዳማ ቡና ጋር ስማቸው እየተያያዘ ይገኛል፡፡ ከነዚህ መካከል ከሀዋሳ ከተማ የለቀቀው ተስፉ ኤልያስ ለመፈረም የተቃረበ ሲሆን ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ኢስማኤል ዋቴንጋ የመቆየቱ ጉዳይ አጠራጣሪ የሆነው ለአለም ብርሀኑን ሊተካ እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ኄኖክ ካሳሁን እና ግርማ በቀለም ስማቸው ከሲዳማ ጋር የተያያዘ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የለቀቁ ተጫዋቾች

ወደ ድሬዳዋ ከተማ ያመሩት ሳውሬል ኦልሪሽ ፣ አንተነህ ተስፈዬ ፣ ሰንደይ ሙቱኩ ፣ ኤሪክ ሙራንዳ እና ወሰኑ ማዜ ክለቡን የለቀቁ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *