የክልል ክለቦች ሻምፒዮና 5ኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና 5ኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ የጁ ፍሬ እና ናኖ ሁርቡ ወደ ተከታዩ ዙር ያለፉበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

ምድብ 1

የዚህ ምድብ ጨዋታዎች መልካ ቆሌ ላይ ሲደረጉ የጁ ፍሬ ወልዲያ ያሬድ ምስጋናው ባስቆጠረው ጎል ታግዞ ኢተያን 1-0 በማሸነፍ ከወዲሁ ወደ 2ኛው ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በዚሁ ምድብ ቀደም ብለው ጨዋታቸውን ያደረጉት ሾኔ ከተማ እና ሽረ እንዳስላሴ ቢ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ምድብ 2

ከምድብ ሀ ጨዋታዎች በመቀጠል በተደረገው የዚህ ምድብ ጨዋታ ቡሬ ከተማ ቤንች ማጂ ፖሊስን 1-0 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ኮተን መተከል ፖሊስን 2-0 አሸንፏል፡፡ ምድቡን ድሬዳዋ ኮተን 7 ፣ መርካቶ አካባቢ እና ቡሬ ከተማ 4 ነጥቦች በመያዝ የማለፍ ተስፋ የያዙ ቡድኖች ናቸው፡፡

ምድብ 3

በወልድያ መምህራን ኮሌጅ በተደረጉት ጨዋታዎች አሳሳ ከተማ ከ ደጋን ከተማ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ ናኖ ሁርቡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስን 1-0 አሸንፏል፡፡ ድሉን ተከትሎ የአዲስ አበባው ናኖ ሁርቡ በ6 ነጥቦች ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡

ምድብ 4

በመሐመድ አላሙዲ በተደረጉት የዚህ ምድብ ጨዋታዎች አረካ ከተማ እና ሰንዳፋ በኬ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል፡፡

በ8:00 በተደረገው ጨዋታ አረካ ከተማ ንስርን 1-0 አሸንፏል፡፡ ጨዋታው በተቀዛቀዘ ሁኔታ የጀመረ ሲሆን በአረካ ተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ እንቅስቃሴ ምክንያት በፊሽካ የሚቆራረጥ ነበሮ፡፡ የኋላ ኋላ በአረካ ድንቅ እንቅስቃሴ በታጀበው ጨዋታ 39ኛው ደቂቃ ላይ ሶፎኒያንስ ተሾመ ያስቆጠራት ግብ አረካን ለድል አብቅታለች፡፡

ቀጥሎ በተካሄደው ጨዋታ ሰንዳፋ በኬ ዋልያን 3-1 አሸንፏል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ ሰንዳፋ በኬዎች በዳንኤል ደሳለኝ ግብ መሪ መሆን ሲችሉ ጫና መፍጠራቸውን በመቀጠል በ32ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ከድር ናስር አስቆጥሮ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። በ41 ደቂቃ ደግሞ ዮሀንስ ጌታቸው ፍጥነቱን ተጠቅሞ ባስቆጠረው ሶስተኛ ግብ  ታግዘው ሰንደሰፋዎች በ3–0 መሪነት ለእረፍት ወጥተዋል።
ከእረፍት መልስ ዋልያ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ተጠጭነው የተጫወቱ ቢሆንም በተጨማሪ ደቂቃ በኤርሚያስ ቴዎድሮስ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ልዩነታቸውን ከማጥበብ በቀር ውጤቱን መቀልበስ ሳይችሉ ቀርተዋል።


ውድድሩ ነገም የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይህን ሊንክ ተጭነው ሙሉውን መርሀ ግብር ፣ ውጤት እና ሰንጠረዥ ያገኛሉ፡–  የክልል ክለቦች ሻምፒዮና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *