ለአሰልጣኝ ከማል አህመድ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ ሊደረግ ነው  

በኢትዮጲያ እግር ኳስ ታሪክ ከሚጠቀሱ ውጤታማ አሠልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑት አሰልጣኝ ከማል አህመድ ላቋቋሙት የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከል የገቢ ማሰባሰብያ ጨዋታዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ እሰከ ሐምሌ 29 ድረስ ይቀጥላል፡፡

በሁለቱም ጾታ 150 በላይ ታዳጊዎችን ያቀፈው የማሰልጠኛ ማዕከል ከ13 ፣ 15 እና 17 ዓመት በታች ታዳጊዎችን በመያዝ ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እውቅና አግኝቶ የተቋቋመ ሲሆን ራሱን በገቢ ለማጠናከር የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡

ባሳለፍነው ሰኞ በአሠልጣኝ ከማል አካዳሚ ውስጥ እና በሀዋሳ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የታዳጊ ፕሮጀክቶች መካከል ውድድር የተጀመረ ሲሆን ዛሬም በሀዋሳ ከተማ ውስጥ በሚገኙ አራት የጤና እግርኳስ ቡድኖች መካከል በሚደረግ ውድድር ቀጥሏል፡፡ በቀጣይም የቀድሞ ተጫዋቾች ጨዋታ እና በሚድያዎች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች ይኖራሉ ተብሏል፡፡

የገቢ ማሰባሰብያ መርሀግብሩ ማጠቃለያ የሚሆነውና ከፍተኛ ትኩረት የሳበው በመጪው ቅዳሜ ነሀሴ 29 ቀን 2009 በሀዋሳ ከተማ ስታድየም (ሰው ሰራሽ ሳር) በአሰልጣኙ ስር ተጫውተው ባለፉ ተጫዋቾች መካከል የሚደረገው ጨዋታ ነው፡፡ በመጀመርያው ቡድን ውሰጥ ከ1989-1993 በሀዋሳ ከተማ ቆይታቸው በአሰልጣኙ ስር የሰለጠኑ ተጨዋቾች እንደነ ገረሱ ሸመና ፣ አፈወርቅ ዮሐንስ ፣ ያሬድ አበጀ ፣ ዘውዱ በቀለ ፣ ሰብስቤ ደፋር ፣ ብርሃኑ ጉታ ፣ አንዱአለም አረጋ እና አለማየሁ ሞላ ሲካተቱ ከ1993 ወዲህ እስከ አሁን ድረስ ባሉት አመታት በአሰልጣኙ የሰለጠኑት አዳነ ግርማ ፣ ሽመልስ በቀለ ፣ ሙሉጌታ ምህረት ፣ በኃይሉ አሰፋ ፣ ግርማ በቀለ ፣ በረከት ይስሀቅ እና ሌሎች ተጫዋቾች በሁለተኛው ቡድን ውስጥ ተካተዋል፡፡

በ1971 የደቡብ ኢትዮጵያ እርሻ ሰብል አሰልጣኝ በመሆን ወደ አሰልጣኝነት ሙያ የገቡት ከማል አህመድ ሀዋሳ ከተማ ከተመሰረተበት 1978 ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ክለቡ አሁን ላለበት ደረጃም መሰረት የጣሉ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ በ1996 እና 1999 የሊግ ፣ በ1997 ደግሞ የጥሎ ማለፍ ቻምፒዮን መሆን የቻሉ ሲሆን በሰበታ ከተማ ፣ ኒያላ ፣ ውሀ ስፖርት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ሰርተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *