የሴቶች ዝውውር | አዳማ ከተማ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሊጉ ክስተት ከነበሩ ቡድኖች አንዱ የነበረው ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ የተገኙ ወጣት ተጫዋቾችን ከአንጋፋ ተጫዋቾች በማጣመር የተገነባው አዳማ ከተማ በቀጣይ አመት ይበልጥ ተጠናክሮ ለመቅረብና ለሊጉ ዋንጫ በብርቱ የሚፎካከር ቡድንን ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ሀ ጠንካራ ተፎካካሪ ከመሆን ምድቡን በሁለተኛነት አጠናቆ በማጠቃለያው ጨዋታ ላይ ሀዋሳ ከተማን በመርታት በሊጉ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ የቻለው አዳማ ከተማ አምስት ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጥሩ ብቃትዋን ያሳየችውን ግብጠባቂዋን እምወድሽ ይርጋሸዋን ጨምሮ የበርካታ የቡድኑን ቋሚ ተጫዋቾችን ውል ያደሱት አዳማ ከተማዎች በድሬዳዋ ከተማ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት አጥቂዎቹ ይታገሱ ተክለወርቅ እና ድንቅነሽ በቀለ ፣ ተከላካይዋ ዝናቧ ሽፈራው ፣ ያለፉት ሁለት አመታት በሀዋሳ ከተማ ያሳለፈችው አማካይዋ ፅዮን ሳህሌ እንዲሁም በጥረት ኮርፖሬት (ቀድሞ ዳሽን ቢራ) መልካም ጊዜያት ማሳለፍ የቻለችው የመስመር አጥቂዋ ሠርካለም ጉታን ማስፈረማቸው አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በቀጣዮቹ ጊዜያት ሁለት ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾች ለማስፈረም ቡድኑ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *