ባምላክ ተሰማ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታ እንዲመራ ተመርጧል

ኢትዮጵያዊው የፊፋ ኢንተርናሽናል የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ቅዳሜ መደረግ በሚጀምረው የካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ እንዲመራ ተመርጧል፡፡ ባምላክ በነሃሴ ወር በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ሊበርቪል ላይ ኮትዲቯር ጋቦንን 3-0 ያሸነፈችበትን ጨዋታ መምራት መቻሉ የሚታወስ ነው፡፡

በመጪው እሁድ ከሚጠበቁት ጨዋታዎች መካከል ቅድሚያውን የያዘው የወቅቱ አፍሪካ ቻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከሞሮኮው ቻምፒዮን ዋይዳድ ካዛብላንካ ጋር የሚያደርጉት የሉካስ ማስተርፒስስ ሞሪፔ ስታዲየም ጨዋታ ባምላክ ተሰማ በመሃል ዳኛነት የሚመራ ይሆናል፡፡ የባምላክ ረዳቶችም ኦሊቨር ሳፋሪ ካቤኔ ከዲ.ሪ. ኮንጎ እና ማርክ ሶንኮ ከዩጋንዳ ሁነዋል፡፡ ረዳት ዳኞቹ ከዚህ ቀደም እንደባምላክ ሁሉ የጋቦን እና የኮትዲቯር ጨዋታን የመሩ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ዳኞች በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ የነበራቸው ተሳታፊነት እየቀዘቀዘ የመጣ ቢሆንም ከቅርብ አመታት ወዲህ ባምላክ፣ ዘካሪያስ ግርማ፣ ሃይለየሱስ ባዘዘው፣ ሊዲያ ታፈሰ፣ በላይ ታደሰ፣ ክንዴ ሙሴ፣ ተመስገን ሳሙኤል፣ ትግል ግዛው፣ ወይንሸት ካሳዬ እና የመሳሰሉት በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ መዳኘት ችለዋል፡፡ ሊዲያ ታፈሰ ከሌሎቹ በተለየ የፊፋ የዓለም ሴቶች ዋንጫ እና የታዳጊዎች ውድድር ላይ በአርቢትርነት መሳተፍ ችላለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *