ኢትዮጵያ በፊፋ የሃገራት ደረጃ መንሸራተቷን ቀጥላለች

የዓለም አቀፉ የእግርኳስ የበላይ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ በየወሩ የሚያወጣው የሃገራት ደረጃ ዛሬ ይፋ ሲሆን ኢትዮጵያ 24 ደረጃዎች ቁልቁል ወርዳለች፡፡

በነሃሴ ወር በተካሄዱ ጨዋታዎች አማካይነት ደረጃው ሲወጣ በወሩ የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያደረገችው የደርሶ መልስ ጨዋታ በአጠቃላይ ውጤት 2-1 ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሲሆን በወሩ መጨረሻ በፊፋ የወዳጅነት ጨዋታ ፕሮግራም ላይም መሳተፍ አለመቻሏን ተከትሎ ከአለም 24 ደረጃዎችን ወርዳ ከአለም 144ኛ ሆናለች፡፡

የስልጣን ዘመኑ በማብቃት ላይ ባለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አመራር ስር ባለፉት አራት አመታት ይህ ደረጃ መጥፎ የሚባለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ 31 ደረጃዎችን ከወረደችው ጓቲማላ ቀጥሎ በወሩ በከፍተኛ መጠን የደረጃ ማሽቆልቆል ያሳየች ሁለተኛዋ ሃገር በመሆንም ባሳለፍነው ወር ከነበራት 259 ነጥብ ወደ 191 ነጥብ ወርዳለች፡፡

በሴቶች ደረጃ በሴካፋ ሴቶች ቻምፒዮና ከተሳተፈ በኃላ ከውድድር የራቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ1143 ነጥብ የደረጃ ለውጥ ሳያሳይ 93ኛ ላይ ይገኛል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ቢቀርቡለትም ፌድሬሽኑ አዎንታዊ መልስ ባለመስጠቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከሴካፋ ዞን ሃገራት ዩጋንዳ ከዓለም 71ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ግብፅ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ስትሆን ቱኒዚያ፣ ሴኔጋል፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ እና ናይጄሪያ እስከ5 ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ካሜሮን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጋና፣ ኮትዲቯር እና ሞሮኮ እስከ10 ያለውን ደረጃ የያዙ ናቸው፡፡

በአለም አቀፉ ደረጃ ጀርመን በሰንጠረዡ አናት ላይ ስትቀመጥ ብራዚል፣ ፖርቹጋል፣ አርጀንቲና፣ ቤልጂየም፣ ፖላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ቺሊ እና ኮሎምቢያ እስከ10 ያለውን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *