ቅድመ ውድድር ዝግጅት  – ኢትዮዽያ ቡና

ኢትዮዽያ ቡና በድጋሚ ወደ ክለቡ በተመለሱት አሰልጣኝ ፖፓዲች እየተመራ በሀዋሳ ከተማ ሴንትራል ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

በ2003 የውድድር ዘመን ከ13 አመታት ጥበቃ በኋላ የሊጉ ቻምፒዮን ከሆነ በኋላ የተሳካ የውድድር አመታት ማሳለፍ ያልቻለ ሲሆን በርካታ አሰልጣኞች ወደ ቡድኑ በማምጣትና በየአመቱ በሚቀያየር የቡድን ስብስብ መረጋጋት የተሳነው ቡድን ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በ2009 የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ከ30 ጨዋታ 12 አሸንፍ ፣ 6 ተሸንፎ 12 ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ 25 ጎል ተቆጥሮበት 36 ጎል አስቆጥሮ በ48 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 5ኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል።

በዘንድሮ የውድድር አመት ኢትዮዽያ ቡና በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የማናያቸው ተጨዋቾች ዮሐንስ በዛብህ (ግብጠባቂ) ፣ አብዱልከሪም መሀመድ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ ሳዲቅ ሴቾ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ያቡን ዊልያም ናቸው።

ክለቡ በክረምቱ በርካታ ዝውውሮችን የፈጸመ ሲሆን ከሌሎች ክለቦች በተለየም በርካታ የከፍተኛ ሊግ ተጫዋቾችንም አስፈርሟል፡፡ ወንድወሰን አሸናፊ ( ግብጠባቂ/ ወላይታ ድቻ ) ፣ ቶማስ ስምረቱ ( ተከላካይ/ወላይታ ድቻ ) ፣ አለማየሁ ሙለታ (ተከላካይ / አአ ከተማ) ፣ ሮቤል አስራት ( ተከላካይ/ጅማ ከተማ ) ፣ ትዕግስቱ አበራ ( ሀላባ ከተማ/ተከላካይ ) ፣ ሳምሶን ጥላሁን (አማካይ / ደደቢት) ፣ ክሪዚስቶም ንታንቢ (ጅማ አባ ቡና/ አማካይ) ፣ አስራት ቱንጆ (አመካይ / ጅማ ከተማ) ፣ አብዱሰላም አማን ( አጥቂ /ወልዋሎ) ፣ ማናዬ ፋንቱ (አጥቂ/ ኤሌክትሪክ) ፣ በረከት ይስሃቅ (አጥቂ /ድሬደዋ ከተማ) ክለቡን የተቀላቀሉ ሲሆኑ ከሀምበሪቾ የፈረሙት በረከት አድማሱ እና ድንቅነህ ከበደ በውሰት ለአአ ከተማ እና ሀምበሪቾ በውሰት ተሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በክረምቱ የዝውውር መስኮት ውዝግቦች ያስከተሉ ዝውውሮች ላይ ተሳትፏል፡፡ ከነዚህ መካከል ክሪዚስተቶም ንታንቢን ከአዳማ ጋር ተፎካክሮ ሲያስፈርም ክለቡን ለቆ ለሀዋሳ ከተማ ፈርሞ የነበረው ወንድይፍራው ጌታሁንንም ውል ማደስ እንደሚችል በፌዴሬሽኑ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአክሊሉ አየነው ዝውውር ዙርያ ከፋሲል ከተማ ጋር የይገባኛል ጥያቄ አንስተው ጉዳዮ በኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየታየ የሚገኝ ሲሆን ጉዳዩ እልባት ያላገኘ ቢሆንም ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ተቀላቅሎ ዝግጅት እየሰራ መሆኑን መመልከት ችለናል።

ከተስፋው ቡድን 9 ተጫዋቾች ለዋናው ቡድን ሙከራ ተጠርተው የነበረ ቢሆንም አሰልጣኙን በማሳመን ቡድኑን ተቀለቅለው እየሰሩ ያሉት አዲስ በቄ (ግብ ጠባቂ) እና አብዱልበሲጥ ከማል ናቸው፡፡

በአጠቃላይ 29 ተጨዋቾች በሙሉ ሆቴል ገብተው ከነሐሴ መጀመርያ አንስቶ ዝግጅታቸውን በሚገባ እያከናወኑ ሲገኙ አስቻለው ግርማ እና ሚኪያስ መኮንን በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ጋር እየሰሩ አይገኙም። ኢኮ ፌቨር ደግሞ በዲሲፒሊን ምክንያት ከቡድኑ ውጪ በመሆን አዲስ አበባ እንደሚገኝ ሰምተናል።

በልምምድ ጊዜ ለሁለት ተከፍለው ባደረጉት ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ጨዋታ ለማየት እንደቻልነው ስሜት በተሞላበት መልኩ ጠንካራ ፉክክር ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን ሦስት ተጨዋቾች መጠነኛ ጉዳት አጋጥሟቸው ጨዋታውን አቋርጠው ሲወጡ ተመልክተናል።

አሰልጣኝ ፖፓዲችን በረዳትነት እንዲያገለግሉ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማን በአንድ አመት ኮንትራት ከቡድኑ ጋር ሲያቆይ የቀድሞ የኢትዮዽያ ቡና ተጨዋች ሀብተወልድ ደስታ ሌላው ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመ ሌላው አሰልጣኝ ነው ።

አሰልጣኝ ፓፓዲች ለሶከር ኢትዮዽያ በሰጡት አስተያየት ዝግጅታቸውን አስቀድመው መጀመራቸው ጥሩ ቢሆንም ሁሉም ተጨዋቾች ተሟልተው በጊዜ አለመግባታቸው በስራቸው ላይ እክል እንደፈጠረ ገልፀዋል፡፡ በቡድን ግንባታቸው ላይ አስቀድመው ወደ ኢትዮዽያ ቡና እንዲመጡ ፈልገው የነበሯቸው ተጨዋቾች ወደ ሌላ ክለብ ማምራታቸው እና ሁለተኛ ተመራጭ ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡

ጠንካራ የቅድመ ውድድር ጊዜ እያሳለፉ እንደሆነ የገለጹት ፖፓዲች በቡድኑ ዝግጅት ወቅት ታዳጊ ተጨዋቾቹ በሚያሳዩት እንቅስቃሴ እንደተገረሙ ገልፀው በሁለት የተከፈለ አማራጭ ቡድን እንዳዘጋጁ በሂደት ቋሚ አስራ አንድ ተጨዋቾችን ለጨዋታ ለማዘጋጀት እየሰሩ እንደሆነ ፣ የቋሚ ተሰላፊነት እድል ለማግኘት የሚያደርጉት ፉክክር ቡድኑን ውጤታማ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ አክለውም በሂደት ከስብስባቸው ሦስት ተጨዋቾች ሊቀነሱ እንደሚችሉ ጠቆም አድርገው አልፈዋል።

ኢትዮዽያ ቡና የቅድመ ዝግጅቱ መለኪያ የሆነውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በየትኛው ውድድር እንደሚያደርግ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም ከክለቡ አካባቢ እየወጡ ያሉ መረጃዎች በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ሊሳተፍ እንደሚችል ተሰምቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *