​ቅድመ ውድድር ዝግጅት – ወልዲያ 

ወልዲያ የዋና አሰልጣኝ ለውጥ አድርጎ እና በርካታ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ አካቶ መቀመጫውን ሀዋሳ ከተማ ገዛኸኝ አበራ ሪዞርት ላይ በማድረግ ቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። 

ወልዲያ በ2007 ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ መቀላቀል ችሎ የነበረ ቢሆንም የመጨረሻውን ደረጃ በመያዝ በመጣበት አመት ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ይታወቃል። በ2008  በአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ እየተመራ በምድብ ሀ በከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው አንድም ጨዋታ በሜዳው መልካ ቆሌ ሳይሸነፍ ፋሲል ከተማን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም መቀላቀል ችሏል።

በ2009 በነበረው የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ቆይታው ከ30 ጨዋታዎች 9 ሲያሸንፍ 11 ተሸንፎ 10 ጨዋታን በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ 18 ጎል ሲያስቆጥር 20 ጎል ተቆጥሮበት በ37 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በዚህም ብዙ ጎል የማይቆጠርበት ፣ ብዙ ጎልም ከማያስቆጥሩ  ቡድኖች አንዱ ነበር ።

ክለቡ በ2010 ለሚኖረው የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ክለቡን ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ ብዙ ለውጥ አድርጓል። ወልዲያን ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም እንዲመለስ ካደረጉት ከአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል ።

ከወልድያ ጋር የተለያዩት ተጨዋቾች ዳዊት አሰፋ (ግብ ጠባቂ) ፣ ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ ፣ ያሬድ ዘውድነህ ፣ ቢንያም ዳርሰማ ፣ አለማየሁ ግርማ ፣ ሙሉነህ ግርማ ፣ ዮሐንስ ሀይሉ ፣ ሙሉጌታ ረጋሳ እና ጫላ ድሪባ ሲሆኑ በተጨማሪም የተወሰኑ ተጨዋቾችም ሊቀነሱ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል ።

በ2010 በወልዲያ ማልያ የምንመለከታቸው አዲስ ፈራሚዎች ደረጄ አለሙ ( ግብጠባቂ/አአ ከተማ) ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ ( ተከላካይ/ ጅማ አባቡና) ፣ ታደለ ምህረቴ ( ተከላካይ/ጅማ አባቡና) ፣  ተስፋዬ አለባቸው ( አማካይ/ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ምንያህል ተሾመ ( አማካይ/ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ሰለሞን ገ/መድህን ( አማካይ/ፋሲል ከተማ) ፣ ፍፁም ገ/ማርያም ( አጥቂ/ኢትዮ ኤሌትሪክ) ሲሆኑ ብሩክ ቀልቦሬ ለሁለት ክለብ መፈረሙን ተከትሎ ላቀረበው የይቅርታ ጥያቄ የኢትዮዽያ እግር ኳስ  ፌዴሬሽን በቅርቡ ውሳኔ የሚሰጥ ይሆናል ተብሎ ሚጠበቅ ሲሆን ምን አልባት ብሩክ ወደ ወልዲያ ከተቀላቀሉ ተጨዋቾች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይገመታል ።

ወልድያን ከከፍተኛ ሊጉ የተቀላቀሉ ተጨዋቾች ብርሃኔ አንለይ ( ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት) እና ተስፋሁን ሸጋው ( ባህርዳር) ሲሆኑ ተስፋሚካኤል  በዛብህ በውሰት ከሄደበት ደሴ ከተማ ወደ ወልዲያ የተመለሰ ተጨዋች ነው  ።

ከውጭ ተጨዋቾች ኤደም ኮድዞ ( አጥቂ/ፋሲል ከተማ)  ክለቡን የተቀላቀለ አዲስ ተጨዋች ሲሆን ከወልድያ ጋር የሚያቆያቸውን ተጨማሪ  ውላቸውን ካራዘሙት አዳሙ መሀመድ እና ግብ ጠባቂው ኤሚክሪል ቤሊንጌ በተጨማሪ አንድ የውጪ ዜግነት ያለው ተጨዋች ሙከራ እያደረገ ይገኛል።

በምክትል አሰልጣኝ ኃይማኖት እየተመሩ ከነሐሴ 20 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ገዛኸኝ አበራ ሪዞርት ማረፊያቸውን አድርገው ልምምዳቸውን እያከናወኑ ሲገኝ በቡድኑ ዝግጅት ወቅት እንደተመለከትነው ምንያህል ተሾመ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ፍፁም ገ/ማርያም በበዓልና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ከቡድኑ ጋር አይገኙም፡፡ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ  ይልማ ከበደ ( ጃሬ) በቅድመ ዝግጅት ወቅት በድንገት ባጋጠመው ከፍተኛ ህመም ምክንያት ለተሻለ ህክምና አአ የሚገኝ መሆኑንም ሰምተናል።
ይህን ዝግጅት ባጠናከርነበት ወቅት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ለስልጠና ካቀኑበት ሞሮኮ መመለሳሳቸውን ተከትሎ ከነገ ጀምሮ ቡድኑን በመያዝ ስራቸውን እንደሚጀምሩ አውቀናል።

ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የወልዲያ ምክትል አሰልጣኝ ኃይማኖት ግርማ የዝግጅት ጊዜያቸውን በአግባቡ እያሳለፉ መሆናቸውን ተናግረው አምና በነበረው የፕሪምየር ሊግ ውድድር ጥንካሬዎች ቢኖሩትም ጎል የማስቆጠር እና ከሜዳ ውጭ የማሸነፍ ችግሮችን ዘንድሮ ለማረም አቅም ያላቸውን ተጨዋቾች ወደ ቡድኑ ማምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በ2010 ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን እንቀርባለንም ብለዋል፡፡
ወልዲያ የቡድኑ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ይረዳው ዘንድ በየትኛው የክልል ውድድር እንደሚሳተፍ እስካሁን አለመታወቁ ክለቡ ገልፆልናል።


ምንጭ ካልጠቀስን በቀር በድረ-ገፁ ላይ የሚወጡ ፅሁፎች በሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ፅሁፉን ለህትመት ፣ ለኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎች እና ለድረ-ገፆች ሲጠቀሙ ምንጭ በመጥቀስ ለስራችን ዋጋ ይስጡ

እናመሰግናለን !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *