​ጋቶች ፓኖም ለመጀመርያ ጊዜ በተሰለፈበት ጨዋታ አንዚ ተሸንፏል

የሩሲያ ዋንጫ አንደኛ ዙር ጨዋታዎች መደረግ ሲጀምሩ ከደቂቃዎች በፊት ወደ ቪላዲቮስቶክ ያቀናው አንዚ ማካቻካላ 2-0 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ጋቶች ፓኖምም በክለቡ ማልያ የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታውን አድርጓል፡፡
በክረምቱ ወደ ሩሲያ ያመራው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አማካይ በተለያዩ የአንዚ ጨዋታዎች ላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ለመጀመርያ ጊዜ የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ከመግባቱ በተጨማሪ ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጫውቷል፡፡ በ28ኛው ደቂቃ ላይም ከማዕዘን የተሻማ ኳስን በግምባር ገጭቶ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡

በጨዋታው የተሻሉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ሊች ቭላዲቮስቶኮች አሸናፊ የሆኑባቸውን ጎሎች በ20ኛው ደቂቃ ጎርዲዬንኮ እንዲሁም በ68ኛው ደቂቃ ላይ ማሊያካ አስቆጥረዋል፡፡

አንዚ ማካቻካላ በውጤት ቀውስ ላይ ይገኛል፡፡ 14 ክለቦች በሚወዳደሩበት የሩሲያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ከወዲሁም የአሰልጣኝ ለውጥ አድርጓል፡፡ አንዚ በ11ኛው ሳምንት የሩሲያ ፕሪምየር ሊግ ወደ ሞስኮ ተጉዞ ስፓርታ ሞስኮን የሚገጥም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *