​ቅድመ ውድድር ዝግጅት – ጅማ አባጅፋር 

አዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ጅማ አባ ጅፋር በአሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ እየተመራ አዲስ ቡድን በመገንባት እና የመጠርያ ስም ማሻሻያ በማድረግ በአዳማ ራስ ሆቴል ማረፍያውን አድርጎ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል። 

በ1970 የተመሰረተው ጅማ አባ ጅፋር (ጅማ ከተማ) አዲስ መልክ በ2006 ከተቋቋመ ጀምሮ ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን በ2009 የውድድር አመት ውጥኑ ሰምሮለት በከፍተኛ ሊግ በምድብ ለ ከምድቡ አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቅ  ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ መግባቱን አረጋግጧል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የከፍተኛ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን በውድድር አመቱ የተሳካ  አመት ማሳለፉ ይታወቃል።

ጅማ አባ ጅፈር በ2010 ፕሪምየር ሊግ ለሚኖረው ተሳትፎ ጠንካራ ስራ እየሰራ ሲሆን ከአሰልጣኝ መኮንን ወ/ዮሐንስ ጋር ተለያይቶ በምትኩ በፕሪምየር ሊጉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለውቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል፡፡ በርከት ያሉ ነባር ተጫዋቾቹን አሰናብቶ ከፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ በዛ ያሉ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ በመቀላቀል በአዳማ ከተማ በአዳማ ራስ ሆቴል መቀመጫውን አድርጎ በአዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ በቀን ሁለት ጊዜ ጠንካራ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

በከፍተኛ ሊግ በ2009 ከጅማ ከተማ ጋር አብረው ከነበሩ ተጨዋቾች መካከል ቢንያም ታከለ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ ብሩክ ተሾመ ፣ ተመስገን ገ/ኪዳን ፣ ንጋቱ ገ/ስላሴ ፣ ሮባ ወርቁ እና ዝናቡ ባፋአ ከክለቡ ጋር አብረው የሚቆዮ ሰባት ተጨዋቾች ናቸው።

ከኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀሉ አዲስ ፈራሚዎች ዳዊት አሰፋ ( ግብጠባቂ/ ወልድያ) ፣ ኄኖክ አዱኛ ( ተከላካይ/ድሬደዋ ከነማ) ፣ ቢኒያም ሲራጅ ( ተከላካይ/ ንግድ ባንክ)  ፣ ኄኖክ ኢሳይያስ ( ተከላካይ/ጅማ አባቡና) ፣ ዮናስ ገረመው ( አማካኝ/ንግድ ባንክ) ፣ አሸናፊ ሽብሩ ( አማካይ/ኢትዮ ኤሌትሪክ) ፣ ይሁን እንደሻው ( አማካይ/ድሬደዋ ከተማ) ፣ ጌቱ ረፌራ ( አጥቂ/ንግድ ባንክ) ናቸው፡፡

ከከፍተኛ ሊግ ደግሞ ሦስቱም ተጨዋቾች ከሀድያ ሆሳዕና የመጡ ሲሆን እነሱም አሚን ነስሮ (ተከላካይ) ፣ እንዳለ ደባልቄ (አጥቂ) ፣ ሳምሶን ቆልቻ (አጥቂ) ናቸው ።

እስካሁን በሙከራ ወቅት በእንቅስቃሴው አሰልጣኝ ገብረ መድህን አሳምኖ መፈረም የቻለው የውጭ ሀገር ተጨዋች ሲሴኮ የተባለ ማሊያዊ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ነው፡፡ ሮቲሚ ( ግብ ጠባቂ / ናይጄሪያ) ፣ ሊጋኒ ( ተከላካይ/ቡርኪናፋሶ) ፣ ዴቪድ ሰንደይ ( አጥቂ/ናይጄሪያ) የተባሉ ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር በሙከራ ላይ ሲሆኑ በተለይ ዛሬ ከቡድኑ ጋር የመጀመርያ ልምምዱን ያደረገው ግብጠባቂው ሮቲሚ ያሳየው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ እና በዚህ እንቅስቃሴው የሚቀጥል ከሆነ ሊፈርም እንደሚችል  አሰልጣኝ ገብረመድህን ተናግረዋል፡፡

አዲስ ፈራሚው ሲሴኮ

ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጥሩ የዝግጅት ወቅት እያሳለፉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ” ዝግጅታችንን በአዳማ ከተማ  ከማድረጋችን በፊት ከ15 ቀናት በላይ በጅማ ከተማ ነበር ስንዘጋጅ የቆየነው፡፡ ወደ አዳማ ከተማ ከመጣን ስምንተኛ ቀናችን ሆኗል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ ምንም ልምምዳችንን የማቋረጥ ነገር አላጋጠመንም ፤ የአየር ንብረቱም ጥሩ ነው። ያአሉትም ተጨዋቾች ያላቸው የስራ ፍላጎት ተነሳሽነታቸው መልካም የሚባል ነው። ሆኖም የተጫዋቾች ቁጥራችን ትንሽ ነው።  ከመጀመርያው ጀምሮ ከፍተኛ ሊጉ በቶሎ አለመጠናቀቁ የምልመላ ስራችን በምንፈልገው መንገድ መሄድ አላስቻለንም ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የምታስባቸው ተጫዋቾች ወደ ሌላ ክለብ ይሄዳሉ። አሁን ከቡድኑ ጋር ያሉት 22 ተጨዋቾች ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የቡድኑ አባላት የሆኑት 16 ተጨዋቾች ናቸው፡፡ የተቀሩት 6 ተጨዋቾች ገና ሙከራ እያደረጉ ነው። እንግዲህ ከባድ ነው በእንደነዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ መሆን፡፡ በዛሬው እለት ትንሽ ተስፋ ሰጪ ለውጥ ያየነው ናይጄራዊ ግብ ጠባቂ ጥሩ ነገር አሳይቶናል፡፡ ይህ ደግሞ ለክለቡ ጥሩ ዜና ነው። ከዛ ውጭ አንድ የማሊ ተከላካይ አለ በተጨማሪ እኛ ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፎ የመኖርያ ፍቃድ ባለማግኘቱ ሄዶ ያልተመለሰ የውጭ ሀገር ተጨዋች አለ፡፡ በአጠቃላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው ” ብለዋል፡፡

በሙከራ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች

አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ቡድኑን በቀጣዮቹ ቀናት ለማጠናከር እንደሚፈልጉ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ” ከሀገር ውስጥ ነጥረው የወጡ ለቡድኑ ይጠቅማሉ ብለን የምናስባቸው ካሉ ወደ ክለቡ ለማምጣት እንቀሳቀሳለን፡፡ ከውጭም ቢሆን ብዙ ተጨዋቾች መጥተው እዚህ ካሉት በምንም የማይሻሉ ሆነው በመገኘታቸው ወደመጡበት መልሻለው፡፡ አሁንም እየሞከርን ነው ያሉትም የተሻሉ ከሆኑ እናስፈርማለን፡፡ ካልሆነ ሌሎችን አምጥተን እንሞክራለን” ሲሉ ገልጸው የገጠማቸውን ፈተና ለማለፍ እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡

“ከታች የመጡ ቡድኖች በየጊዜው የሚያስቸግር ችግር ነው፡፡ ይህም ስጋት እንዳይመጣ መጠንቀቅ እንዳለብኝ አስባለው፡፡ የመውረድ ነገር እንዳይመጣ በጥንቃቄ እየሰራን ነው የምንገኘው፡፡ ያሉት ተጫዋቾች የታክቲክ አረዳዳቸው ጥሩ ነው። ያም ቢሆን ብዙ ስራ እንደሚጠበቅብኝ አውቃለው”

ጅማ አባጅፋር የቡድኑን ወቅታዊ አቋም ለመለካት ይረዳው ዘንድ በአአ ከተማ ዋንጫ ወይም አሁን ክለቡ ባልገለፀው ውድድር ላይ ሊሳተፍ እንደሚችል ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *