​” በሁለተኛው ዙር ወደ ሜዳ እመለሳለሁ ” አዲሱ ተስፋዬ

በ2004 የከፍተኛ ሊግ ክለብ ተሳታፊ በሆነው ስልጤ ወራቤ የእግር ኳስ ህይወቱን ጀምሯል። ከሁለት አመታት በኃላም ወላይታ ድቻን በመቀላቀል መልካም ሁለት የውድድር ዘመናትን ካሳለፈ በኋላ በ2008 ወደ መከላከያ አምርቶ በመጫወት ላይ ይገኛል። አዲሱ ተስፋዬ በክለቡ አዲስ ኮንትራትን ቢፈርምም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን መጨረሻ በደረሰበት ጉዳት ያለፉትን ስድስት ወራት ከሜዳ ርቋል። የመሀል ተከላካዩ አዲሱ ስለገጠመዉ ጉዳት እና ቀጣይ ሁኔታውን ለሶከር ኢትዮጵያው ቴዎድሮስ ታከለ ነግሮታል።

ረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቅክበት ጉዳት ምን ነበር ? መቼ ነበር ያጋጠመህ ?

በ2009 የፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታን ይርጋለም ላይ ከሲዳማ ቡና ስናደርግ ነበር ጉዳት የገጠመኝ። ጉዳቱ ደግሞ የጉልበት (በህክምና አጠራሩ ሜኒስከስ) ነው። ሌሎች ከባድ የጉልበት ህመሞች አሉ። ይሄኛው ግን ቀለል ያለ ነው። ከፍተኛ ጉዳት ባይኖረውም ስሜቱ ከበድ ያለ ነበር። በዚህም ምክንያት በዮርዳኖስ ሆስፒታል የMRI ምርመራን ካደረኩ በኃላ በስተመጨረሻም ቀዶ ጥገና አድርጌያለሁ።

ከሜዳ ከራቅክ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖሀል። እናም መቼ ወደ ሜዳ ትመለሳለህ? 

ከሜዳ ከራቅሁ ወደ ስድስት ወር አልፎኛል። አሁን በእርግጥ ቀለል ያለ ልምምድን ጀምሬያለሁ። አሁን ላይ በትኩረት የአካል ብቃት ስራዎችን እየሰራሁ ሙሉ በሙሉ እያገገምኩ እገኛለሁ። ህክምናዬንም እየጨረስኩ ነው፡፡ የህመሙ ስሜትም በመጥፋት ላይ በመሆኑ በሁለተኛው ዙር ወደ ሜዳ እመለሳለሁ።

አንተ በጉዳት ከመከላከያ ጋር አሁን ላይ ጨዋታዎችን ባታደርግም የዘንድሮውን የቡድኑን ጉዞ ከሚያስመዘግበው ውጤት አንፃር እንዴት አየኸው?

የመከላከያ የዘንድሮ አጀማመራችን ደካማ ነበር። ደካማ ብቻም ሳይሆን ወጣ ገባ አቋም እና ውጤት እያመጣን ነው ያለነው። ቡድናችን ጥሩ አይደለም ፤ መጥፎም አይደለም። በጊዜ ሂደት በመስራት ይፈታል ብዬ አስባለሁ፡፡

ቀጣይ እቅድህ ምንድነው ?

በፍጥነት ወደ ቋሚ 11 ውስጥ መግባት የመጀመሪያ ፍላጎቴ ነው። በቅርብ ጊዜም ይሄ ይሆናል። በመከላከያ የነበረኝን ነገር እመልሰዋለሁ ይህም ፤ ሩቅ አይሆንም።

በመከላከያ አሁን ሶስተኛ አመቴ ነው። ዘንድሮ ውሌን አድሻለው። ጠንክሬ በመስራት ወደፊት ሀገሪቱ ውስጥ ትልቅ በሚባሉት ክለቦች ውስጥ መጫወት እፈልጋለሁ። ከዛም አልፎ በብሔራዊ ቡድንም በተደጋጋሚ ተጠርቻለሁ። ነገር ግን የመጫወትን እድል አላገኘሁም። በቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ለመሰለፍ እጥራለሁ። የውጭ እድሎች አሁን ላይ ሰፍተዋል ብዙ ተጫዋቾች ከሀገራችን እየወጡ ነው። እኔም ያንን አድል ለማግኘት ጠንክሬ እሰራለሁ፡፡

በክረምቱ ስምህ ከበርካታ ክለቦች ዝውውር ጋር ሲያያዝ ነበር። ሆኖም በመከላከያ ለመቀጠል ፈርመሀል። የተለየ ምክንያት ይኖርህ ይሆን ?

መከላከያን የመረጥኩበት ምክንያት ክለቡ ነፃነት ያለበት ቡድን ስለሆነ ነው። ሁሉንም ነገር ጠይቀህ የማታጣበት ቤት ነው። ነፃነቱ በጣም ደስ ይላል። ያን ፈልጌ ነበር እዚሁ ልቀጥል የቻልኩት። ጉዳት ላይ ብሆንም በትዕግስት የጠበቀኝ ክለብ ነው።

በመጨረሻ…

ከሁሉም በፊትፈጣሪን እያመሰገንኩ በጉዳቴ ወቅት ከጎኔ ለነበሩት በተለይ የመከላከያ ስፖርት ክለብን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። ውል በምጨርስበት አመት ላይ ሆኜ ጉዳት አጋጥሞኝ አልጋ ላይ በነበርኩበት ወቅት ተመልሶ ያገለግለናል በማለት አምነውብኝ ስለስፈረሙኝ ምስጋናዬ የጎላ ነው። ጉዳት ገጥሞህ ማንም ክለብ አያስፈርምህም ፤ መከላከያ ግን በዚህ ከባድ ወቅቶ ይህን አስበው እንድቀጥል ስለረዱኝ ደጋግሜ አመሰግናለሁ፡፡

የሜኒስከስ ጉዳት ዝርዝር

(በሳሙኤል የሺዋስ)

የሜኒስከስ ጉዳት በጉልበት መገጣጠሚያ የሚገኙት የግማሽ ጨረቃ ቅርፅ ያላቸው ሁለት ሜኒስኪ የተባሉ የሰውነት አካላት መቀደድ የሚያስከትለው ጉዳት ነው። እነዚህ ሁለት አካላት የመሃለኛው (medial) ሜኒስከስ እና የዳርኛው (lateral) ሜኒስከስ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ስሪታቸውም ጠንካራ ሆኖ የመተጣጠፍ ባህሪ ካለው ልስልስ አጥንት (fibrocartillage) ነው። በጉልበት ላይ የሚያርፈውን የሰውነት ክብደት ተቀብሎ መበተን፣ በመዞር እና በመሽከርከር እንቅስቃሴ ወቅት የጉልበት መገጣጠሚያን ማረጋጋት እና የመገጣጠሚያ አጥንቶቹን ፍትግያ የመቀነስ ስራ በነዚህ አካላት ይከወናል።

የሜኒስከስ መቀደድ አብዛኛውን ጊዜ እግር መሬት ላይ ባረፈበት ወቅት ለመዞር ወይም ለመሽከርከር በሚደረግ የእንቅስቃሴ ሂደት ይከሰታል። ይህን መሰል እንቅስቃሴ በሚስተዋልባቸው እንደ እግርኳስ ባሉ ስፖርቶችም የዚህን አካል ጉዳት መመልከት የተለመደ ነው። በጉልበት ላይ የሚያርፍ እና ጉልበት ወደ ውስጥ እንዲታጠፍ የሚያደርግ የወጪ ሃይል ይህንን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በእርግጥ በእድሜ በገፉ ሰዎች ላይ በሜኒስከሶቹ መዋቅር መዳከም ምክኒያት ያለምንም አካላዊ አደጋ ወይም በአነስተኛ ንክኪ ምክኒያት ጉዳቱ ሊፈጠር ይችላል። የሜኒስከስ መቀደድ ብቻውን ወይም የጉልበት መገጣጠሚያን እንቅስቃሴ ከሚያረጋጉት የክሩሺዬት እና ኮላተራል ጅማቶች ጉዳት ጋር ተደምሮ ይከሰታል።

በጉዳቱ ምክኒያት የሚፈጠረው ህመም የሚለያይ ሲሆን ከአነስተኛ ጉዳት በኋላ የሚፈጠረው ቀላል የህመም ስሜት ተጫዋቾች እንቅስቃሴያቸውን ወዲያውኑ እንዲያቋርጡ ላያስገድዳቸው ይችላል። ከጉዳቱ በኋላ ባለው የአንድ ቀን ጊዜ ውስጥ ግን በጉልበት አካባቢ የህመም ስሜት እና የመገጣጠሚያው ማበጥ ያጋጥማል፤ ህመሙም በተለይ የመዞር እና የመሽከርከር እንቅስቃሴ በሚደረግበት ጊዜ የሚባባስ ነው። ለጊዜው ከጠፋ በኋላ ስፖርተኛው ወደ እንቅስቃሴ ሲመለስ አብሮ የሚመለስ ህመም፣ የጉልበት መገጣጠሚያ እንቅስቃሴ መገደብ እና የመገጣጠሚያው የሰውነት ክብደትን መሸከም አለመቻል የሜኒስከስ ጉዳት ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

እግርኳስ ተጫዋቾች ይህን ጉዳት ሙሉ በሙሉ መከላከል ባይችሉም እንዳይደርስ ግን ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይችላሉ። በጉልበት ዙሪያ የሚገኙ ጡንቻዎችን የሚያገዝፉ እና የሚያጠነክሩ እንቅስቃሴዎችን መስራት ጡንቻዎቹ ለመገጣጠሚያው ተጨማሪ ድጋፍ እና ከለላ እንዲሆኑ ያስችላል። ሜኒስከስን የሚጫኑ እንደ ቁጭ ብድግ አይነት እንቅስቃሴዎችን ሲሰሩ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ከልምምድ እና ጨዋታ በፊት በቂ የሰውነት ማሟሟቂያ እና ማፍታቻ እንቅስቃሴዎች ማድረግ እና የጉልበት መከላከያ ቁሶችን መጠቀም ጉዳቱን የሚከላከሉ መንገዶች ናቸው።

የዚህ ጉዳት ቀዳሚ የህክምና አማራጭ እረፍት ማድረግ ነው። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና በመገጣጠሚያው ላይ የሚያርፈው ክብደትን መቀነስ (አስፈላጊ ከሆነ ክራንች መጠቀም) ወሳኝ ነው። ቀን በእረፍት እና ሌሊት በእንቅልፍ ጊዜ በጉልበት መገጣጠሚያ ስር ትራስ በማድረግ መደገፍ፣ ጉዳቱ ባጋጠመ በመጀመሪያ ቀናት በየ4 ሰዓት ልዩነት ለ15 ደቂቃዎች ያህል በረዶ በመገጣጠሚያው ላይ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደ ጉዳቱ መጠን በህክምና ባለሞያዎች ውሳኔ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ጉዳቶችም ይኖራሉ። ያለ ቀዶ ጥገና በቂ ህክምና ያገኙ ተጫዋቾች ከ6 እስከ 8 ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መመለስ የሚችሉ ሲሆን የቀዶ ጥገና ህክምና የተደረገላቸው ተጫዋቾች በአንፃሩ ወደ እግርኳስ ለመመለስ ከ3-4 ወራት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *