ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

100ኛ የእርስ በርስ ግንኙነት ጎል በገለልተኛ ሜዳ እንደሚቆጠር በሚጠበቅበት የሀዋሳ እና የጊዮርጊስ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል። 

ከ1991 ጀምሮ ለሊጉ ቤተኛ የነበረው የአሰላ ስታዲየም ሙገር ሲሚንቶ በ2007 ከወረደ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ነገ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታን ያስተናግዳል። ከደቡብ ፖሊስ እና ድቻ ጨዋታ አስቀድሞ የተፈጠረውን የጋፊዎች ጥቃት ተከትሎ በነበረው ውጥረት ነው ይህም ጨዋታ ሳይካሄድ ለነገ 09፡00 ወደ አሰላ የተዘዋወረው። ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ አዳማ ላይ ሦስት ነጥቦችን አሳክተው የተመለሱት ሀዋሳዎች መጠነኛ እፎይታ አግኝተዋል። ሆኖም አሁንም ያሉበት የ9ኛ ደረጃ አጥጋቢ ባለመሆኑ የነገውን ከባድ ጨዋታ በማሸነፍ ሦስት ደረጃዎችን የማሻሻል ዕድላቸውን መጠቀም ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ሲዳማን በመርታት በመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያሳኩበትን መጥፎ ጉዞ ማሻሻል የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ከመሪው ጋር ያላቸውን የ12 ነጥቦች ልዩነት ለማጥበብ ከጨዋታው የሚገኙት ነጥቦች በእጅጉ ያስፈልጓቸዋል።

ታፈሰ ሰለሞንን በግል ጉዳይ ዳንኤል ደርቤን ደግሞ በድንግተኛ ህመም መጠቅም ባይችሉም በምንተስኖት አበራ እና ብሩክ በየነ ክፍተቱን በመሸፈን አዳማ ላይ ባሳኩት ድል ሳቢያ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ የተጫዋች ምርጫ ላይ ይቸገሩ እንደሆን እንጂ ነገም ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። በዚህም በድኑ በዋነኝነት ከመስመር የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶችን ባማከለ ሁኔታ እንደሚያጠቃ ሲጠበቅ ከእስራኤል እሸቱ እና የቀድሞው ክለቡን የሚገጥመው አዳነ ግርማ ተሻጋሪ ኳሶችን የመጠቀም ብቃት በተጨማሪ ከጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮች የሚሰጠውም ምላሽ በእጅጉ ተጠባቂ ነው። ሀዋሳዎች ገብረመስቀል ዱባለን በጉዳት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በቅጣት ሲያጡ አዲስአለም ተስፋዬ ደግሞ ቅጣቱን ጨርሶ ይመለስላቸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት የፊት አጥቂዎችን በተጠቀመበት የሲዳማው ጨዋታ ያስመዘገበው ድል በዛው አኳኋን እንዲቀጥል የሚያደርገው ይመስላል። የወትሮውን ከባድ የመስመር ጥቃት አስፈሪነት መልሶ ማግኘት ችሎ የነበረው የአሰልጣኝ ስትዋት ሀል ቡድን ነገም አማካይ ክፍል ላይ በሦስትዮሽ ጥምረቱ በሚፈልገው ደረጃ ኳስ መያዝ የሚያስችለውን ነፃነት ላያገኝ ቢችልም ከተጋጣሚው የሚመጣበትን የመስመር ጥቃት በተመሳሳይ አካሄድ ለመመለስ እንደሚጥር ይገመታል። የወጣት አጥቂዎቹ ፍጥነትም ከሀዋሳ ሦስት የመሀል ተከላካዮች ጎን ክፍተቶችን ለመጠቅም ሊረዳው ይችላል። ቡድኑ ወሳኝ ተከላካዩ አስቻለው ታመነን በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ሲያጣ በተቃራኒው ሳላዲን በርጌቾ ከቅጣት ይመለስለታል። ከዚህ ውጪ መሀሪ መና ፣ ሳላዲን ሰዒድ ፣ ጌታነህ ከበደ እና ምንተስኖት አዳነ አሁንም ከጉዳታቸው አላገገሙም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ክለቦቹ በሊጉ 39 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 24 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ 7 ጊዜ ድል ሲቀናቸው ቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 67 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 31 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

– የሁለቱ ክለቦች ግንኙነት በድምሩ 98 ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ያለግብ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የግቦቹ መጠን ነገ 100 እንደሚደፍን ይጠበቃል።

ዳኛ

– መቐለ እና ድቻ ባደረጉት ጨዋታ በ4ኛ ዳኝነት የተመደበችው እና የሳምንቱን የባህር ዳር እና መቐለ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመራችው ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በዚህ ጨዋታ የመሀል ዳኝነት ኃላፊነት ተሰጥቷታል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

አዲስዓለም ንጉሴ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – ታፈሰ ሰለሞን – ሄኖክ ድልቢ– ምንተስኖት አበራ – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ኄኖክ አዱኛ – ሳላዲን በርጌቾ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ኢሱፍ ቡርሀና

ናትናኤል ዘለቀ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀምፍሬይ ሚዮኖ

ሪቻርድ አርተር – አቤል ያለው – አቡበከር ሳኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡