የከፍተኛ ሊግ አጫጭር መረጃዎች

ቅሬታዎች

* ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና ከሻሸመኔ ባደረጉት ጨዋታ ሻሸመኔዎች ጨዋታውን አቋርጠው በመውጣታቸው ካፋ ቡና በፎርፌ ውሳኔ (ሶስት ነጥብ እና ሶስት ጎሎችን) ማግኘቱ ይታወቃል። በተቃራኒው ደግሞ በጨዋታው ለተፈፀመው የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ካፋ ቡና የሜዳው ሁለት ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወት ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ይግባኝ በመጠየቁ ውሳኔው በእግዳ ላይ ይገኝ ነበር። ዛሬ በወጣው መረጃ ደግሞ ካፋ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕና በመጪው እሁድ የሚደርገው የ18ኛ ሳምንት ጨዋታ በወልቂጤ ሜዳ እንዲከናወን ውሳኔ ተላልፏል።

ይህን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በውሳኔው ዘግይቶ መታወቅ ችግር እንደፈጠረባቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ እንደገለፁት በዘንድሮ ውድድር ዓመት የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ በተሻለ መልክ እየመራ የሚገኝ ቢሆንም ውሳኔዎች ላይ መዘገየት እንደሚታይበት ተናግረዋል። ” ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔን ቶሎ ባለማስተላለፉ ምክንያት ቡድናችን ወደየት ተጉዞ እንደሚጫወት አናውቅም ነበር። ይገባኝ ከተባለ ቢያንስ ከ15 ቀን በላይ ሆኖታል፤ ውሳኔውን ለማስተላለፍ ለምን እንደሚቆይ ግን ግልፅ አይደለም። ወልቂጤ እንድንጫወት ዛሬ ላይ ውሳኔ ተላልፏል። በውሳኔው ዘግይቶ መድረሱ ምን ያህል ቡድኖችን በሥነ-ልቡና ዝግጅትም ሆነ በአቅም እንደሚዳክም መታወቅ መቻል አለበት። ይህም ግንዛቤ ውስጥ ለምን እንደማይገባ አላውቅም።” ብለዋል።

*የከፍተኛ ሊግ ውድድር ወደ መጠናቀቂያው እየተቃረበ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ተሳታፊ ቡድኖች በዳኝነቱ ላይ ቅሬታቸው እያሰሙ ይገኛሉ። በቅርቡ እንኳን በዳኝነት ውሳኔ ላይ ኢትዮጵያ መድን፣ ኢኮስኮ እና ዲላ ከተማ ቅሬታቸውን የገለፁ ሲሆን በተለይም በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ እና ሀምበሪቾ ጨዋታ ላይ በነበረው ዳኝነት ላይ የአዲስ አበባ ስራ ከተማ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ እንዲሁም የቡድን አባላት ደስተኛ እንዳልነበሩ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ እንደገለፁም ታውቋል።

ሰበታ ከተማ

በምድብ ሀ ከአናት የተቀመጠው ሰበታ ከተማ ከ2003 በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ እየተንደረደረ ይገኛል። በ17 ሳምንት 35 ነጥብ መሰብሰብ የቻለው ሰበታ ከተማ ባሳለፍነው እሁድ ከአቃቂ ቃሊቲ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ተከላካዩ ታደለ ባይሳን በቀይ ካርድ ያጣ ሲሆን በውድድር ዓመቱ 10 ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን በጣምራ እየመራ የሚገኘው ናትናኤል ጋንቹላ ጉዳት አጋጥሞታል። ይህም የቡድኑን ጉዞ ፈታኝ እንዳያደርገው ተሰግቷል። ሆኖም የቡድኑ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ቡድኑ በሌሎች ተጫዋቾች ክፍተቶችን በመሸፈን መሪነታቸውን እንደሚያስጠብቁ ተናግረዋል።

ሐብታሙ ታደሰን ተዋወቁት

ስም፡ ሐብታሙ ታደሰ
ቁመት፡ 1.83
ክብደት፡ 71 ኪ.ግ
ክለብ፡ ወልቂጤ ከተማ
የሚጫወትበት ቦታ፡ አጥቂ፣ አማካይ

በቡሌ ሆራ ከተማ የተወለደው ሐብታሙ በአንደኛ ሊግ በሚወዳደረው የከተማው ክለብ (ቡሌ ሆራ) የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረ ሲሆን ከአምና ጀምሮ ለወልቂጤ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል።

ሐብታሙ በከፍተኛ ሊጉ ዘንድሮ ዘጠኝ ጎሎች ያስቆጠረ ሲሆን 10 ጎሎች ካስቆጠሩ ሦስት ተጫዋቾች ዝቅ ብሎ ለሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት መፎካከር ጀምሯል። ተጫዋቹ እንደሌሎች ተፎካካሪዎቹ ጎሎቹን ያስቆጠረው በበርካታ ጨዋታዎች ሳይሆን በሁለት ጨዋታ ብቻ፤ አንድ ቡድን ላይ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል። ናሽናል ሴሜንትን በመጀመርያው ዙር ድሬዳዋ ላይ 7-1 ሲያሸንፉ ሐት-ትሪክ የሰራ ሲሆን በ17ኛው ሳምንት ባቱ ላይ በተመሳሳይ ናሽናል ሴሜንትን 7-2 ሲረቱ ስድስት ጎሎችን አስቆጥሮ በከፍተኛ ሊግ ታሪክ የመጀመርያው ተጫዋች መሆን ችሏል። ” የተጫወትኩት ስድስት ጨዋታ ነው። እንደ እድል ሆኖ በሁለት ጨዋታ ላይ 9 ግቦችን አግብቻለሁ። ሁኔታው አስገራሚ ነው፤ ደስተኛም አድርጎኛል። ሆኖም ከዚህ በላይ እኔን የሚያስደስተኝ ቡድኔ ውጤታማ መሆኑ ነው። በእኔ እምነት ይህ አጋጣሚ ነው። በቀጣይ ጠንክሬ በመስራት ከዚህ በላይ ግቦችን ማስቆጠር ነው የምፈልገው። ” ሲል ስለ ሁኔታው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

የ18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር

(ሁሉም ጨዋታዎች እሁድ ይካሄዳሉ)

ምድብ ሀ

ሰበታ ከተማ 9:00 ገላን ከተማ
አክሱም ከተማ 9:00 ለገጣፎ ለገዳዲ
ፌዴራል ፖሊስ 9:00 ደሴ ከተማ
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 9:00 ቡራዩ ከተማ
አውስኮድ 9:00 አቃቂ ቃሊቲ
ወሎ ኮምቦልቻ 9:00 ወልዲያ

ምድብ ለ

ሀምበሪቾ 9:00 ድሬዳዎ ፖሊስ
ዲላ ከተማ 9:00 ወልቂጤ ከተማ
ነጌሌ አርሴ 9:00 ናሽናል ሲሜንት
ኢኮስኮ 9:00 ኢትዮጵያ መድን
ሀላባ ከተማ 9:00 የካ ክ/ከተማ
ወላይታ ሶዶ 9:00 አዲስ አበባ ከተማ

ምድብ ሐ

ካፋ ቡና 9:00 ሀዲያ ሆሳዕና (ወልቂጤ)
ነቀምት ከተማ 9:00 ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ
ነጌሌ ቦረና 9:00 ካምባታ ሺንሺቾ
ሻሸመኔ ከተማ 9:00 አርባምንጭ ከተማ
ቤንች ማጂ ቡና 9:00 ስልጤ ወራቤ
ቡታጅራ ከተማ 9:00 ጅማ አባ ቡና


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡