ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ባህር ዳር ከተማ

ነገ በብቸኝነት በትግራይ ስታድየም በዝግ የሚካሄደውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከሳምንታት በኃላ ወደ ልምምድ ተመልሰው ያለፉት አራት ቀናት በቋሚነት ልምምድ የሰሩት ሰማያዊዎቹ በፕሪምየርሊጉ የመቆየታቸው ጉዳይ ያበቃለት ቢመስልም ቡድኑ ከረጅም ጊዜ የደሞዝ ጥያቄው መመለስ በኃላ የሚያደርገው ጨዋታ በመሆኑ በተሻለ ተነሳሽነት ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፉት ጨዋታዎች በጉዳት እና ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ተወጥረው ሁለተኛው ዙር በጀመሩበት ቅኝትና የማሸነፍ መንፈስ መቀጠል ያቃታቸው ደደቢቶች ከወልዋሎ ጋር በነበረው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው መድሃኔ ብርሃኔ ቅጣት ውጪ ሙሉ ቡድናቸው በመልካም ጤንነት በማግኘታችው በሁለተኛው ዙር በአመዛኙ ከተጠቀሙበት የመጀመርያ አሰላለፍ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ሁለተኛው ዙር ዓመቱን በጀመሩበት ጥሩ የማሸነፍ ጉዞ ማስቀጠል የተሳናቸው አዲስ አዳጊዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ምንም እንኳ ከዋንጫ ፉክክሩም ሆነ ላለመውረድ ከሚደረገው  ትግል ነፃ ሆነው ወደዚህ ጨዋታ ቢቀርቡም ባለፉት ጨዋታዎች ጉዳት ላይ የነበሩ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾች ውስጥ የተወሰኑትን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸውን ተከትሎ በጨዋታው ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። የተጫዋቾችን በርካታ ጉዳት ተከትሎ ከተፈጥሮአዊ ቦታቸው በመቀየር እና በማፈራረቅ ለመጠቀም  የተገደዱት የጣና ሞገዶቹ በነገው ጨዋታም ስምንት የሚደርሱ የቡድኑ ተጫዋቾች ከጉዳት ባለመመለሳቸው በአጨዋወትም በአደራደርም ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዓመቱ ቡድኑን በቋሚነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቤል ውዱ ፣ ዳንኤል ኃይሉ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ሣላምላክ ተገኝን ጨምሮ ማራኪ ወርቁ ፣ ዳግማዊ ሙሉጌታ ፣ ቴዎድሮስ ሙላቱ እና ተስፋሁን ሸጋው ባጋጠማቸው ጉዳት በነገው ጨዋታ አይጠቀሙም።

ከጉዳቱ በተጨማሪ ቡድኑ ዛሬ አመሻሽ ወደ መቐለ ከተማ መግባቱ እና በሚጫወትበት ስታድየም ከጨዋታው በፊት ልምምድ አለማድረጉ በነገው ጨዋታ ሊፈትነው እንደሚችል ይገመታል።

የእርሰ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገናኘው  የ10ኛ ሳምንት ጨዋታ በባህር ዳር 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

– ደደቢት በትግራይ ስታድየም ላይ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ሁለት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ በሌሎቹ ተሸንፏል።

– ባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአራቱ ነጥብ ተጋርቶ በስድስቱ ደግሞ ተሸንፎ ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታው በሄኖክ አክሊሉ የመሀል ዳኝነት የሚመራ ይሆናል። በጥቂት ጨዋታዎች በርካታ ጠንካራ ውሳኔዎች ያሳለፈው አርቢትሩ እስካሁን አራት ጨዋታዎችን የዳኘ ሲሆን ስድስት የቢጫ እና ሁለት የቀይ ካርዶችን ሲመዝ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችንም ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1)

ሙሴ ዮሃንስ

ዳግማዊ ዓባይ – ዳዊት ወርቁ – አንቶንዮ አቡዋላ –ሄኖክ መርሹ

የአብስራ ተስፋዬ – ኤፍሬም ጌታቸው

አቤል እንዳለ – አለምአንተ ካሳ – ፉሰይኒ ኑሁ

መድሃኔ ታደሰ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪሰን ሔሱ

ግርማ ዲሳሳ – አሌክስ አሙዙ – ወንድሜነህ ደረጄ  – አስናቀ ሞገስ

ሚካኤል ዳኛቸው – ደረጄ መንግስቱ – ኤልያስ አህመድ

ፍቃዱ ወርቁ – ጃኮ አራፋት – ወሰኑ ዓሊ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡