የአሰልጣኞች አስተያየት | መቐለ 70 እንደርታ 0-1 ሀዋሳ ከተማ

በትግራይ ዓለምአቀፍ ስታድየም ሀዋሳ ከተማ መቐለን 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“የሊጉን መሪ በዚህ ሁሉ ህዝብ ፊት ማሸነፍ የሀዋሳን ጥንካሬ ያሳያል ” አዲሴ ካሳ

ጨዋታው ከመጀመርያውም እንደሚከብደን አውቀን ነበር። ምክንያቱም እነሱም በሁለት ነጥብ ነበር ከተከታያቸው የሚርቁት። እኛም ከታች ያሉት እየደረሱብን ስለሆነ ከነሱ ለመራቅ አስበን ነበር በጥንቃቄ ስንጫወት የነበረው። ያስብነው ነገርም አሳክተናል።

ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ስላለው ውጤት

በዚህ ዓመት ሃዋሳ ከተማ ያሻሻለው ነገር ይሄ ነው።
ከዚ በፊት ከከተማው ውጭ አሸንፎ አያውቅም ነበር። በዚ ዓመት ግን ሶስት ጊዜ አሸንፈናል። ይሄ ደሞ ትልቅ ነገር ነው። ዛሬ የገጠምነው የሊጉ መሪን ነው። ይህን ክለብ በዚህ ሁሉ ህዝብ ፊት ማሸነፍ የሀዋሳን ጥንካሬ ያሳያል። ተደጋጋሚ ሽንፈቶች ነበሩብን እነዛ ሽንፈቶች ደሞ ተፅዕኖ አሳድረውብናል። የሊጉ መሪ በሜዳው ማሸነፍ ትልቅ ነገር ነው። እነሱም ተፅዕኖ ውስጥ እንዳሉ ይገባናል፤ ከኛ በበለጠ ተፅዕኖ ውስጥ ነበሩ። የተሻለ ነገርም አይቼባቸዋለው። ምክንያቱም መጀመርያ ዙር ላይ አሸነፉን እንጂ እንዲህ አልነበረም እንቅስቃሴያቸው። ዛሬ የተሻለ እንቅስቃሴ ነው ያደረጉት። እንዲ አልጠበቅኩም ኳሱን ይዘው ይጫወታሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር።

“እግር ኳስ ነውና በተቀሩት ጨዋታዎች ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም” ገብረመድህን ኃይሌ

ጨዋታው ለኛ ጥሩ አልነበረም። ለመጀመርያ ግዜ ነው በሜዳችን የተሸነፍነው። ካሰብነው ውጭ ነው የሆነው ያለውን የነጥብ ልዩነት አስጠብቆ ለመሄድ የግድ ማሸነፍ ነበረብን። የተፈጠረው ክፍተት ዋጋ አስከፍሎናል። በመጀመርያው አጋማሽ አጥቅተን ባላጋራ ሜዳ ላይ ለመግባት ብዙ ጥረት አድርገናል ሁለተኛው አጋማሽም እንደዛው። ጫና ውስጥ ሆነን ስላደረግነው የችኮላ ውሳኔዎቻችን አስቸግረውናል። ጫናው በዝቷል አንዳንዶቹ ማድረግ የሚችሉትም ማድረግ እየተሳናቸው ነው ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች አግኝተን ነበር መጠቀም አልቻልንም ይህ አንዱ የእግር ኳስ ባህሪ ስለሆነ እንቀበለዋለን።

ስለ መጀመርያው አጋማሽ አጨዋወታቸው

ከዕረፍት በፊት የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩብን።
ተከላካዮች የሚፈጥሩት ስህተቶች ነበሩ የቦታ አያያዝ ነበር ሽፋን የመስጠት ችግርም ይታይ ነበር እሱን ተጠቅመውም የተወሰነ ዕድል ፈጥረው ነበር ጫናው ሲበረታ ብዙ ነገርህን ነው ምታጣው።
ሁለተኛ አጋማሽም በርካታ ዕድሎች ፈጥረን ነበር።

የተቀሩት ጨዋታዎች..

ባለን አቅም ነው የምንቀሳቀሰው። ሌሎች የተጫዋቾች አማራጮችም ለማየት ሞክረናል። ተደጋጋሚ ሽንፈት ስላጋጠመን ግን የአቅም ውስንነት አለ። በማጥቃት ላይ ወሳኝ የሆነ ስራ በመስራት የሚሰራ እምነት የሚጣልበት ተጫዋች ያስፈጋሃል እኛ ደሞ የለንም። በጉልበት እየተበለጡ ነው በፍጥነትም መቀዛቀዝ አለ እነዚ የፈጠሩት ክፍተቶች። እግር ኳስ ነውና በተቀሩት ጨዋታዎች ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡