የአሰልጣኞች አስተያየት | ደቡብ ፖሊስ 1-1 ስሑል ሽረ

በ25ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላለመውረድ እየታገሉ ያሉት ደቡብ ፖሊስ እና ስሑል ሽረን ሀዋሳ ላይ ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱም ክለቦች ከሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

“ብዙ ኳሶች ብረት መልሶብናል ፤ ዕድለኛ አለመሆን ነው እንጂ ጥሩ ነበርን” ገብረክርስቶስ ቢራራ – ደቡብ ፖሊስ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ነበር እነሱ ከዕረፍት በፊት ለ15 ደቂቃዎች ኳስን ተቆጣጥረው ነበር። ከዕረፍት በኋላ ግን አጥቅተን ተጫውተናል ፤ ነገር ግን ግብ ማግባት አልቻልንም። ብዙ ኳሶችን ብረት መልሶብናል ፤ እንግዲህ ዕደለኛ አለመሆን ነው እንጂ ጥሩ ነበርን።”

በመጀመሪያው አጋማሽ ስለታየው ተደጋጋሚ የተከላካዮች ስህተት

“ተጫዋቾቼ አጥቅተው ለመጫወት ስላሰቡ ተዘርዝረው ስለነበር ይህ ነበር ችግራችን። ጨዋታውን ለማሸነፍ ጉጉት ስለነበራቸው ለዛ ነበር ያልተረጋጉት። በሁለተኛው አጋማሽ እነሱም ወደ እኛ ግብ መድረስ ስላልቻሉ ተረጋግተን መጫወት ችለናል።”

በሜዳው ነጥብ ስለመጣሉ

“በዘመናዊ እግር ኳስ በሜዳህ እና ከሜዳህ ውጪ መጫወት የቀረ ይመስለኛል። ምክንያቱም ሁለቱም ዕኩል ናቸው። ለዕለቱ ጨዋታ ብቻ ነው ትኩረት የምንሰጠው።”

ስላልፀደቀችው ኳስ

“ማንም ያየው ነው ፤ ኳሷ መረብ ነክታለች ነገር ግን ኳሱ ፈጣን ስለነበር እኔ ዳኛውን ጥፋተኛ ነህ ብዬ መውቀስ አልፈልግም። እኛ ዳኞችን ከነስህተቶቻቸውም ቢሆን እናከብራለን ፤ ግን ያስቆጫል።”

“ግብ ጠባቂያቸው ያዳነብን በርካታ ኳሶች ከሽንፈት እንዲድኑ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል” ሳምሶን አየለ – ስሑል ሽረ

ስለጨዋታው

“ሁለታችን ካለንበት የወራጅ ቀጠና ስጋት ለመውጣት ያደረግነው ትግል በጣም ከባድ ነበር። ግብ ጠባቂያቸው ያዳነብን በርካታ ኳሶች ከሽንፈት እንዲድኑ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ተጭነው በመጫወት ግብ ማግባትም ችለዋል። እኛም ግብ አግብተን ከሜዳችን ውጪ ነጥብ መጋራታችን በጣም ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ቀጣይ ሳምንት በሜዳችን የመውረድ ስጋት ያለበት መከላከያን ስለምንገጥም የተሻለ ዕድል ይዘን ነው ምንሄደው።”

በመጀመሪያው ግማሽ ስላልተጠቀሙባቸው ዕድሎች

“ትክክል ነው እጅግ ዋጋ እያስከፈለን ነው ያለው። ብዙ ግብ እያገባልን ያለው ሳሊፍ ፎፋና ነው እሱም ያው ሦስት ኳስ ስቷል ፤ የአጥቂም ባህሪ ነው። ግን ያገኘነውን አጋጣሚ የማንጠቀም ከሆነ ካለብን የመውረድ ስጋት አንፃር ዋጋ ያስከፍለናል በዚህ ላይ ጠንክረን እንሰራለን። ”

ቡድኑ በሳሊፍ ፎፋና ላይ ጥገኛ ስለመሆኑ

“እውነት ነው በፎፋና ላይ ብቻ ጥገኛ መሆናችን ነው ዋጋ እያስከፈለን ያለው። ከዛም ባሻገር ከመስመርም ከመሀልም በሚነሱ ኳሶች ዕድሎችን ፈጥረን ግብ አግብተን ነጥብ አስጠብቀን ከችግር የምንወጣበት ነገር ለመፍጠር እንሞክራለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡