ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ሀዋሳን እና ቡናን በሚያገናኘው ጨዋታ ላይ የሚነሱ ዋና ዋና ነጥቦችን እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

ጨዋታው ከነገ ጨዋታዎች መካከል በሁለቱም የሰንጠረዡ ፉክክሮች ውስጥ በማይገኙ ክለቦች መካከል የሚደረግ ብቸኛው ጨዋታ ነው። ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳርን ባስተናገደበት የ19ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ በነበረው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ምክንያት በተላለፈበት ቅጣት ይግባኝ ጠይቆ ቅጣቱ በተቀነሰለት መሰረት ይህ ጨዋታ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ይደረጋል ቢባልም የከተማዋ ፖሊስ ኃላፊነቱን አልወስድም በማለቱ ወደ አሰላው አረንጓዴ ስታድየም ተዘዋውሯል። አምናም ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን አዳማ ላይ ማከናወናቸው ይታወሳል።

ዓመቱን በጀመሩበት ፍጥነት መዝለቅ ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ባልተጠበቀ መልኩ መቐለ 70 እንደርታን በሜዳው ከረቱ በኋላ ነው ለዚህ ጨዋታ የደረሱት። ድሉም በሁለተኛው ዙር ያስመዘገቡት ሁለተኛ ድላቸው ሆኖ ሲመዘገብ ከዚያ አስቀድሞ ነገ ጨዋታቸውን ሊያደርጉ በነበሩበት ስታድየም አዳማን በረቱበት ጨዋታ ነበር ለመጨረሻ ጊዜ ሦስት ነጥብ አሳክተው የነበረው። በሰንጠረዡ አጋማሽ የሚገኘው ቡድኑ ከነገው ጨዋታ የሚያገኛቸው ነጥቦች እስከ ስድስተኛነት ከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ። ሀዋሳዎች አሁንም ታፈሰ ሰለሞን ላይ ያስተላለፉን ቅጣት ያላነሱ ሲሆን ገብረመስቀል ዱባለ ቸርነት አውሽ እና ሄኖክ ድልቢ ደግሞ በጉዳት ምክንያት ነገ የማይጠቀሙባቸው ተጫዋቾች ናቸው።

ኢትዮጵያ ቡናም እንደተጋጣሚው ሁሉ ሊጉን መምራት ጀምሮ ከነበረባቸው ጊዜያት ወርዶ በ33 ነጥቦች አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባህር ዳርን በሰፊ ጎል ከረቱ በኋላ አራት ጨዋታዎችን ያለድል የተጓዙት ቡናማዎቹ ሜዳቸው ላይ በሲዳማ ቡና የደረሰባቸው ሽንፈት ደግሞ ያሉበትን ሁኔታ ከሀዋሳም የባሰ ያደርገዋል። በእርግጥ ነገን በውጤት መመለስ ከቻሉ ሁለት ደረጃዎችን ማሻሻል የሚችሉ ሲሆን የራቃቸውን የድል መንፈስ መልሶ ማግኘት ግን በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። በጨዋታው ለቡና ትልቁ ዜና የአቡበከር ናስር ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ወደ ሜዳ መመለሱ ሲሆን ሚኪያስ መኮንን እና አልሀሰን ካሉሻ ግን አሁንም በጉዳት ወደ አዳማ አለማምራታቸው ታውቋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሊጉ በአዲስ ፎርማት ከተጀመረበት 1990 ጅምሮ ሳይወርዱ የቆዩት ሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ውጤታቸው በመሀላቸው ያለውን የፉክክር ሚዛናዊነት የሚያሳይ ነው። እስካሁን 41 ጊዜ ሲገናኙ በ15 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 14 ሀዋሳ ደግሞ 12 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል።

– ከ1996 ጀምሮ ግብ አልባ ጨዋታ ያላደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በ41 ጨዋታዎቻቸው ኢትዮጵያ ቡና 52 ጊዜ ኳስ እና መረብን ሲያገናኝ ሀዋሳ ከተማም ሶስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 43 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

– ለሁለተኛ ጊዜ በገለልተኛ ሜዳ ጨዋታውን የሚያደርገው ሀዋሳ ከተማ በ21ኛው ሳምንት ከሌላው የመዲናዋ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አሰላ ላይ ያደረገው ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– ለ11ኛ ጊዜ ከአዲስ አበባ ስታድየም ውጪ የሚጫወተው ኢትዮጵያ ቡና ሁለት የድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። ከስድስቱ ሦስቱ አንድ ግብ ብቻ ባስቆጠረባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች የተመዘገቡ ናቸው።

ዳኛ

– ጨዋታው ዘንድሮ ወደ ሊጉ ለመጣው ዮናስ ካሳሁን ሰባተኛው ይሆናል። ዮናስ በመሀል ዳኝነት በተሰየመባቸው ስድስት ጨዋታዎች 26 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመዘዘ ሲሆን ዓመቱን የጀመረው ኢትዬጵያ ቡናን ከድቻ ባገናኘው ጨዋታ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ወንድማገኝ ማዕረግ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – አክሊሉ ተፈራ – ምንተስኖት አበራ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ

ኢትዮጵያ ቡና (4-2-3-1)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ቶማስ ስምረቱ – ተካልኝ ደጀኔ

አማኑኤል ዮሀንስ – ዳንኤል ደምሴ

እያሱ ታምሩ – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ

ሁሴን ሻባኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: