​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ መቐለ 70 እንደርታ

የዛሬው የመጨረሻ ዳሰሳችን ጅማ ላይ የሚደረገው ሌላኛውን ትኩረት ሳቢ ጨዋታ ይመለከታል።

በሁለተኛው ዙር ካሳዩት መጠነኛ መነቃቃት በኃላ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ደረጃቸውን ለማሻሻል የነበራቸውን ሰፊ ዕድል ያመከኑት ቻምፒዮኖቹ ምንም እንኳን በፋሲል ከነማ ከገጠማቸው ሰፊ ሽንፈት በኃላ የሚያደርጉት ጨዋታ ቢሆንም ነገ ሜዳቸው ላይ እንደመጫወታቸው ቀላል ግምት አይሰጣቸውም። ባለፉት ጨዋታዎች 4-4-2 እና 4-3-3 አፈራርቀው የተጠቀሙት ባለሜዳዎቹ አባ ጅፋሮች በቋሚ አሰላለፍ የተጠቀሙባቸው በርካታ ተጫዋቾች በጉዳት ማጣታቸውን ተከትሎ በተጫዋቾች ምርጫም በአደራደርም ለውጥ የሚያደርጉበት ዕድል የሰፋ ነው። በቤተሰብ ጉዳይ ከቡድኑ ተለይቶ ወደ ቤልጅየም በማምራቱ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ያለፈው ዳንኤል አጄይ እና በጉዳት የባለፈው ሳምንት ጨዋታ ያለፈው ኦኪኪ ኦፎላቢ ወደ ሜዳ የሚመለሱ ሲሆን በአንፃሩ ተስፋዬ መላኩ እና ብሩክ ገብርአብ በጉዳት እንዲሁም መስዑድ መሐመድ በግል ጉዳይ ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የአስቻለው ግርማ እና ዐወት ገብረሚካኤል መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳቸው በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት አስተናግደው ከሊጉ መሪነት የወረዱት ምዓም አናብስት ምንም እንኳን መጥፎ የሜዳ ውጪ ክብረ ወሰን ቢኖሯቸውም በነገው ወሳኝ ጨዋታ በርካታ ተጫዋቾች ከጉዳት መልስ ማግኘታቸውን ተከትሎ መጥፎ ክብረወሰኑን የመቀልበስ ዕድል ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በህመም ጨዋታ ያላደረገው ኦሴይ ማውሊን ጨምሮ የአሰልጣኙ ቀዳሚ ምርጫ የሆኑት ፍሊፕ ኦቮኖ እና ክዌኩ አንዶህ ከጉዳት መልስ ማግኘቱን በአጨዋወት ላይ በርካታ ለውጦችን ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቁማል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ረጅሙ አጥቂያቸውን በጉዳት ማጣታቸውን ተከትሎ የሚታወቁበት ረጃጅም ኳሶች ላይ የተመሰረተውን ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ለመተግበር የተቸገሩት መቐለዎች አጥቂው ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው አጨዋወታቸው ወደነበረበት ለመመለስ እንደሚረዳቸው ይታመናል። ከተመለሱላቸው ተጫዋቾች ውጪ ግን በእንግዶቹ ቤት የተሰማ የቅጣት እና ጉዳት ዜና የለም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በ2010 የውድድር ዓመት ሊጉን የተቀላቀሉት መቐለ እና ጅማ በተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በየሜዳቸው የ1-0 ድልን ማስካት ሲችሉ ዘንድሮ ደግሞ መቐለ በሜዳው 2-1 አሸንፏል።

– ጅማዎች በሜዳቸው 12 ተጋጣሚዎችን ያስተናገዱ ሲሆን ሽንፈት ሳይገጥማቸው ስድስቱን በድል ስድስቱን ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

– መቐለ 70 እንደርታ እስካሁን አስር የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ሲያከናውን በመጀመሪያ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ አቻ በመውጣት ከዚያም ሦስት ተከታታይ ድሎችን ቢያስመዘግብም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎቹ ደግሞ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ለመምራት የተመደበው ብርሀኑ መኩሪያ እስካሁን በዳኘባቸው ሰባት ጨዋታዎች 25 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት እና አንድ የሁለተኛ ቢጫ ካርድ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፍሊፕ ኦቮኖ

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተስማ – ክዌኩ አንዶህ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል መሐመድ – ሚካኤል ደስታ

ያሬድ ከበደ – ሀይደር ሸረፋ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ኦሴይ ማውሊ

ጅማ አባጅፋር (4-4-2) 

ዳንኤል አጄይ

ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ዲዲዬ ለብሪ – ዋለልኝ ገብሬ – ይሁን እንዳሻው – ፈሪድ የሱፍ

ማማዱ ሲዲቤ – ኦኪኪ ኦፎላቢ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡