የሴቶች ሁለተኛ ዲቪዝዮን የ2011 የውድድር ዓመት በአቃቂ ቃሊቲ ቻምፒዮንነት ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን የ2011 የውድድር ዘመን ቅዳሜ ፍፃሜውን ሲያገኝ አቃቂ ቃሊቲ ቻምፒዮን ሆኗል።

በመዝጊያው ዕለት የዋንጫ እድል የነበራቸው አቃቂ ቃሊቲ እና መቐለ 70 እንደርታ በተመሳሳይ 4 ሰዓት ጨዋታዎቻቸውን ያከናወኑ ሲሆን አቃቂ ቃሊቲ ፋሲል ከነማን 3-2 አሸንፎ ቻምፒዮንነቱን አረጋግጧል። የአሸናፊነት እድሉ በአቃቂ ቃሊቲ ነጥብ መጣል ላይ ተሞርኩዞ የነበረው መቐለ ደግሞ ወደ ሻሸመኔ አምርቶ 3-2 ተሸንፏል።

በአዲስ አበባ ስታድየም የተደረገው የአቃቂ ቃሊቲ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በበርካታ የባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች ደምቆ የተካሄደ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት ተጀምሯል። በፈጣን እንቅስቃሴ እና ተደጋጋሚ የግብ አጋጣሚዎች ጨዋታውን የጀመሩት አቃቂዎች በሠላም ኃይሌ አማካኝነት ተደጋጋሚ እድሎችን ፈጥረዋል። በ4ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ገብታ በመምታት ብረት የመለሰባት ሠላም ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ከግራ የሳጥኑ ክፍል በጥሩ ሁኔታ የመታችው ኳስ ከመረብ አርፎ አቃቂን ቀዳሚ አድርጋለች። ብዙም ሳይቆይ ለፋሲል ተከላካዮች ፈታኝ የነበረችው ሠላም በቀኝ በኩል ገብታ የመታችው ኳስ አቅጣጫ ስቶ እየሩስ ታደሰ ጋር ደርሶ ሁለተኛው ጎል ተቆጥሯል።

ከጎሎቹ በኋላ ቀስ በቀስ የተቀዛቀዘው ጨዋታ በቀሪዎቹ የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎች የግብ እድል ለመፍጠር ከሚደረግ ሙከራ ውጪ ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ጠንካራ ሙከራ ሳይታይበት ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ፋሲል ከነማዎች የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ተሽለው መቅረብ የቻሉ ሲሆን በ62ኛው ደቂቃ ሜሮን ዘሪሁን ምንትዋቦችን ወደ ጨዋታ የምትመልስ ጎል አስቆጥራ ልዩነቱን አጥብባለች። በቀጣዮቹ 20 ደቂቃዎች ጨዋታው አንዴ ፈጠን አንዴ ቀዝቀዝ ብሎ ቀጥሎ በ82ኛው ደቂቃ ዙፋን ደፈርሻ የመታችውን ቅጣት ምት ግብ ጠባቂዋ ስትመልሰው ዓይናለም መኮንን አግኝታ ወደ ጎልነት በመቀየር የአቃቂን መሪነት መልሳ አስፍታለች። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ እስከዳር አወቀ ፋሲልን ከሽንፈት ያልታደገች ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በአቃቂ ቃሊቲ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ሦስተኛ ለወጣው ፋሲል ከነማ የነሀስ ሜዳልያ እንዲሁም ለቻምፒዮኑ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የወርቅ ሜዳልያ እና ዋንጫ በእለቱ የክብር እንግዶች ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን እኛ አቶ ኢብራሂም ሐሰን አማካኝነት ተሰጥቶ የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።

በ8 ክለቦች መካከል ሲካሄድ ከቆየው ከዚህ ውድድር አቃቂ ቃሊቲ እና ተከታይ ሆኖ ያጠናቀቀው መቐለ 70 እንደርታ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ሲያድጉ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቦታቸውን ተክተው በሁለተኛ ዲቪዝዮን ይወዳደራሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: