ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ጎንደር ላይ በሚካሄደው የነገ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በዕኩል ነጥቦች ሊጉን በመምራት ላይ ካሉ ክለቦች መካከል በግብ ልዩነቶች የተሻለ በመሆን ከላይ የተቀመጠው ፋሲል ነገ ባህር ዳርን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በፉክክሩ ውስጥ አንድ እርምጃ ሊያራምደው ይችላል። ከተፎካካሪዎቹ አንዱ ሲዳማ ቡና ዛሬ መሸነፉ እንዲሁም መቐለ 70 እንደርታም ከሜዳው ውጪ መጫወቱ ሲታይ በሜዳው የሚጫወተው ፋሲል የነጥብ ልዩነት ሊፈጥር የሚችልበት ሳምንት እንደሆነ መናገር ይቻላል። በአንፃሩ ለተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ ጨዋታው አንድ ደረጃ አሻሽሎ ወደ ስድስተኛነት ከፍ ከማለት የዘለለ ትርጉም አይኖረውም።

ከአምስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ሳምንት ሶዶ ላይ ሽንፈት የገጠማቸው አፄዎቹ ነገ ሙሉ ኃይላቸውን በማጥቃት ላይ አድርገው እንደሚገቡ ይጠበቃል። በዚህም ለማጥቃት ምቹ ከሆኑት የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቻቸው ባለፈ የመስመር ተከላካዮቻቸውም በነፃነት ወደ ፊት በመሄድ ማጥቃቱን እንደሚያግዙ ይጠበቃል። በመሆኑም ቡድኑን በሦስተኛው የሜዳ ክፍል አስፈሪ እንዲሆን የሚያደርገው የመስመር አጥቂዎቹ እንቅስቃሴም ወደ ተጋጣሚው ሳጥን የጠበበ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው። የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ከሀብታሙ ተከስተ እና አብዱራህማን ሙባረክ ውጪ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች አለመኖሩም ከወገብ በላይ ያለው ክፍሉ እንደወትሮው ሁሉ በአማራጮች የተሞላ ሆኖ ወደ ጨዋታው ይገባል።  በራሳቸው ሜዳ ላይ በመሆን በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን እንደሚፈጥሩ በሚጠበቁት ባህር ዳሮች ደግሞ አምስት ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውንን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያሰልፉም። ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቀውን የቡድኑን አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙን ጨምሮ ኤሊያስ አህመድ፣ አስናቀ ሞገስ፣ ተስፋሁን ሸጋው እና ወሰኑ ዓሊ ወደ ጎንደር ያልተጓዙት የቡድኑ ተጫዋቾች ናቸው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱን ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ያገናኘው የዘንድሮው የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– እስካሁን ጎንደር ላይ ምንም ሽንፈት ያልገጠመው ፋሲል ከነማ ዘጠኝ ድሎች እና አራት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግቧል። ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳው ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎችም ዘጠኝ ግቦች አስቆጥሮ አንድ ግብ በማስተናገድ ሙሉ ዘጠኝ ነጥቦች አሳክቷል። 

– ባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአምስቱ ነጥብ ተጋርቶ በስድስቱ ደግሞ ተሸንፎ ተመልሷል። ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈውም በሰባተኛው ሳምንት ደቡብ ፖሊስን በገጠመ ጊዜ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ከባህር ዳር ውጪ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች 11 ግቦች ተቆጥረውበት ያለነጥብ ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታው ኢንተናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን በድቻ እና ቡና ጨዋታ ከተላለፈበት ቅጣት መልስ የሚመራው ጨዋታ ነው። አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች 30 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን አንድ ተጨዋችም በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ አስወጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ኤፍሬም አለሙ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪሰን ሔሱ

ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – ግርማ ዲሳሳ 

ዳግማዊ አባይ – ደረጄ መንግስቱ – ዳንኤል ኃይሉ

ፍቃዱ ወርቁ – ጃኮ አራፋት – ልደቱ ለማ