ኢትዮጵያ ዋንጫ | አዳማ እና መቐለ ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ ውጤት አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ዋንጫ የአንደኛ ዙር እና ሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች አዳማ እና መቐለ ላይ ተካሂደው አዳማ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ በተመሳሳይ ውጤት ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

አዳማ ላይ አዳማ ከተማን ከ ባህር ዳር ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በባለሜዳው 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በአንፃራዊነት ከባህር ዳር በተሻለ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በጎል ሙከራ ብልጫ የነበራቸው አዳማዎች ቢሆኑም የመጀመርያውን የጎል እድል በመፍጠር ቀዳሚ የነበሩት እንግዶቹ ነበሩ። 16ኛው ደቂቃ ላይ ወሰኑ ዓሊ ከቀኝ መስመር ፍጥነቱን ተጠቅሞ በመግባት 5.50 ውስጥ ለዳግማዊ ሙሉጌታ አቀብሎት አገባው ሲባል ሳይጠቀም ቀርቷል። በባለሜዳዎቹ በኩል በአንድ ደቂቃ ልዩነት 22 እና 23ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ታሪኩ ግልፅ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ የባህርዳሩ ግብጠባቂ ሀሪሰን ሔሱ አድኖበታል።

ባህር ዳሮች ምንም እንኳን ብልጫ ቢወሰድባቸውም ጎል ከማስቆጠር አላገዳቸውም። በመልሶ ማጥቃት 41ኛው ደቂቃ ወሰኑ ዓሊ ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ጃኮ አራፋት ወደ ጎልነት በመቀየር ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ይህች ጎል ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ለነበሩት አዳማዎች በቀሩት አራት ደቂቃዎች እንቅስቃሴቸውን ያወረደው ሆኖ አልፏል።

ከእረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ ተጭነው እንደመጫወታቸው ጎል ማስቆጠርም ችለዋል። 50ኛው ደቂቃ ወጣቱ የመሐል ተከላካይ መናፍ ዐወል ከራሱ የሜዳ ክፍል አንስቶ በአስደናቂ ሁኔታ ከሦስት በላይ ተጫዋቾችን በማለፍ ሳጥን ውስጥ በመግባት ጣጣውን ጨርሶ ያቀበለውን በረከት ደስታ አስቆጥሮ አቻ አድርጓል። ሜዳ ውስጥ ባህር ዳሮች ተዳክመው ሲታዩ በአንፃሩ አዳማዎች የአቻነት ጎል ማስቆጠራቸው የበለጠ መነሳሳትን ፈጥሮላቸው በ66ኛው ደቂቃ በወጣቱ አጥቂ ፉአድ ፈረጃ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ምንም አይነት ጥረት ያላሳዩት ባህርዳሮች ሦስተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደው በ76ኛው ደቂቃ ፉአድ ፈረጃ ያቀበለውን በረከት ደስታ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ቡድኑ ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፉን ተከትሎ ከፋሲል ከነማ ጋር ለግማሽ ፍፃሜ ለማለፍ ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል።

መቐለ ላይ የሊጉ ቻምፒዮን መቐለ 70 እንደርታ የዓምናው የዋንጫው ባለድል መከላከያን 3-1 አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል። በ14ኛው ደቂቃ ከመስመር ሙሉጌታ ያመቻቸለትን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ አስቆጥሮ መቐለን ቀዳሚ ሲያደርግ በ37ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ይድነቃቸው በያሬድ ከበደ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሐይደር ሸረፋ አስቆጥሮ በ2-0 መሪነት ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው ተመስገን ገብረኪዳን በ50ኛው ደቂቃ የኩዌኩ አንዶህ እና ግብ ጠባቂውን አለመናበብ ተጠቅሞ ልዩነቱን ማጥበብ ቢችልም 90ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት የተመታውን ኳስ ይዶነቃቸው ሲተፋው በቅርበት የነበረው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ አስቆጥሮ 3-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡