ኤፍሬም ዘካሪያስ በትውልድ ከተማው ለሚገኝ ፕሮጀክት ድጋፍ አድርጓል

የአዳማ ከተማው አማካይ ኤፍሬም ዘካሪያስ በትውልድ ከተማው መተሐራ (መርቲ) ፋብሪካ ለሚገኝ ታርጌት ለተሰኝ የእግር ኳስ ፕሮጀክት የትጥቅ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በትውልድ ከተማው መተሐራ እግር ኳስን የጀመረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ የአሁኑ የአዳማ አማካይ ኤፍሬም ዘካሪያስ በልጅነቱ ተጫውቶ ባለፈበት ታርጌት የታዳጊ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ቡድን ከባለቤቱ ጋር በስፍራው ተገኝቶ ከ35 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ24 በላይ ቢብሶች፣ 10 ኳሶች፣ 50 ኮኖች እና 25 የመጫወቻ ጫማዎች ድጋፍን አድርጓል፡፡

ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ “እኔ ይህን ሳደርግ ደስ ይለኛል። ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ ካሰብክ ታዳጊዎችን መደገፍህ ግድ ይልሀል። የተሻልን ቦታ ላይ ስንሆን ያሳለፍንበትን መርሳት የለብንም። ይህን ማድረጌን እቀጥልበታለሁ። ዛሬ ከባለቤቴ ጋር የተገናኘሁበት ቀን ናት። ይህን በየዓመቱ ለማሰብም ጭምር ይህን ድጋፍ አደርጋለሁ።” ብሏል፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በትውልድ ከተማቸው ያደጉበትን የእግር ኳስ ክለብ እና ፕሮጀክት በተለያዩ መልኩ እየደገፉ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ጌታነህ ከበደ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ሚካኤል ጆርጅ፣ አብዱልከሪም መሐመድ፣ ኡመድ ዑኩሪ፣ አስቻለው ታመነ፣ ለዓለም ብርሀኑ፣ ሀብቶም ቢሰጠኝ፣ ግሩም ባሻዬ እና አማኑኤል ባሻዬ ከሴቶች ደግሞ ሎዛ አበራ እና ሰናይት ቦጋለ ተመሳሳይ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡