” ጨዋታውን እዚሁ ጨርሰን ለመሄድ ሁላችንም በቁርጠኝነት ተነስተናል። ” ኃይሉ ነጋሽ

የ2011 የኢትዮጵያ ዋንጫን አሸንፎ በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ተሳተፊ የሆነው ፋሲል ከነማ ነገ 10 ሰዓት ላይ በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም የቅድመ ማጣርያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከታንዛኒያው አዛም ጋር ያደርጋል። ስለጨዋታው እና ስለቡድኑ ዝግጅትም ምክትል አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል።

ለጨዋታው ያደረጋችሁት ዝግጅት ?

ዝግጅታችንን ወደ ባህር ዳር ከመጣን ጊዜ አንስቶ ለተከታታይ አስር ቀናት ያከናወንን ሲሆን ከዛ ውስጥ በአምስቱ በቀን ሁለት ጊዜ በመስራት በተቀሩትን ቀናት ደግሞ በቀን አንድ ጊዜ ዝግጅታችንን ስናከናውን ቆይተናል።

ጨዋታው በሜዳችሁ እንደመሆኑ ምን ዓይነት የተለየ የሥነ ልቡና ዝግጅት አድርጋችኋል ?

ጨዋታው በሜዳችን መሆኑ እዚሁ ጨርሰን ለመሄድ ነው የተዘጋጀነው። ተጫዋቾቻችን ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የማሸነፍ ተነሳሽነት በማስቀጠል ዙሪያ የተሻለ ስራ ሰርተናል። ጨዋታውን እዚሁ ጨርሰን ለመሄድ ሁላችንም በቁርጠኝነት ተነስተናል። በጉጉትም እየጠበቅነው ነው።

ከእናንተ በተቃራኒ ተጋጣሚያችሁ በርካታ ጨዋታዎች አድርጓል። ይህ ተፅዕኖ አይኖረውም ?

እኛ ለየት ያለ የወዳጅነት ጨዋታ አላደረግንም።  ከጥሎ ማለፉ የፍፃሜ ጨዋታ በኋላ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ዕረፍት ከሰጠን በኋላ በቀጥታ ወደ ዝግጅት ነው የገባነው። እነሱ በሴካፋ የክለቦች ውድድር ላይ እንደተካፈሉ መረጃው አለን። ከዛም ለፍፃሜ ደርሰው እንደተሸነፉ ሰምተናል ፤ እኛም በበኩላችን በቂ ነው የምንለውን ዝግጅት አድርገናል።

ስለ ተጋጣሚያችሁ ያገኛችሁት በቂ መረጃ አለ?

እንደነገርኩህ ሴካፋ ላይ ለፍፃሜ መድረስ የቻሉበትን አጋጣሚ አይተናል። ክለቡ የራሱ የዩ ቲዩብ ገፅ አለው። እዛ ላይ በርካታ ቪዲዮችን ተመልክተናል። ከዛ በመነሳት ‘ምን ማድረግ አለብን ?’ በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ከተጫዋቾቹ ጋር በመሆን የሚጠበቅብንን ስራ ሰርተናል ።

ጨዋታው በሜዳችሁ ከመሆኑ እንፃር የሜዳ ላይ ዕቅዳችሁ ምንድነው ?

እንደኔ ጨዋታው በሜዳችን መሆኑ ጠቀሜታ አለው። ከዚሁ ጨርሰን ለመሄድ ነው ትልቅ ዕቅዳችን ፤ ግብ እንደይቆጠርብን በጥንቃቄ በመጫወት በተቃራኒው ግቦችን አስቆጥረን ሜዳችን ላይ ጨርሰን ለመሄድ ነው ሀሳባችን።

ለደጋፊው ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት አለ ?

የፋሲል ከነማ ደጋፊ የታወቀ ነው ፤ 12ኛ ተጫዋች ማለት ነው። ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከእኛ ስራ በተጨማሪ ከዚህ በፊት ያደርግ እንደነበረው ሁሉ የደጋፊው እገዛ ያስፈልገናል። 90 ደቂቃ አልቆ ፊሽካ እስከ ሚነፋበት ሰዓት ድረስ ከጎናችን እንዲሆኑ እና ተጫዋቾችን በማበረታታት ቢደግፉን መልካም ነው። እኛም ደግሞ ለማሸነፍ ዝግጁ ነን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡