በ4ኛው የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰብ ሩጫ ዙርያ መግለጫ ተሰጠ

40ሺህ ያኽል ተሳታፊዎች ይካፈሉበታል ተብሎ የሚጠበቀው 4ኛው ዙር የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰብ ሩጫ በመጪው እሁድ ነሐሴ 19 መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ እንደሚካሄድ ተገልጿል። ይህን በማስመልከትም የሩጫው አዘጋጅ ኮሚቴ ዛሬ ከሰዓት በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫው ላይ የሩጫውን አዘጋጅ ኮሚቴ በመወከል አቶ ይስማሸዋ ሥዩም፣ ሰለሞን ታምራትና ክፍሌ አማረን ጨምሮ የውድድሩ አጋር የሆነው ሐበሻ ቢራ በንጉስ ማልት ተወካይ በመሆን በጋራ መግለጫውን ሰጥተዋል፡፡

መግለጫውን የከፈቱትና የሩጫው አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ይስማሸዋ ሥዩም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የክለቦች ወጪን በዘላቂነት ለመቋቋም መሠል የደጋፊውን አቅም ለመጠቀም የሚያግዙ ኹነቶች አይነተኛ ሚና እንዲጫወቱ አውስተው በቀጣይ ከሩጫው በተጨማሪ ሌሎች መርሃግብሮችን ለማዘጋጀት መታቀዱን ተናግረዋል ፤ አያይዘው ክለቡ ለመሰል ሁነቶች ትኩረት በመስጠት በቀጣይም ይህንና ተጓዳኝ ጉዳዮችን በበላይነት የሚቆጣጠርና የሚመራ የሥራ ክፍል ለማቋቋም ስለመታቀዱም ገልጸዋል፡፡

በፈርቀዳጅነት ይህንን ውድድር በማዘጋጀት በ2007 በተደረገውና የመጀመሪያው ዙር 8ሺህ ተካፋዮች ከተሳተፉበት ውድድር አንስቶ በየዓመቱ በተሳታፊዎች ቁጥርም ሆነ በውድድሩ ጥራት እምርታን እያሳየ የመጣው ውድድር መሆኑን ገልፀው በዘንድሮው ውድድር የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 40ሺህ ከፍ በማለቱ ውድድሩ ከዚህ ቀደም ይደረግበት ከነበረው የክለቡ ተጫዋቾች መኖሪያና የቡድኑ የወደፊት ስታዲየም መገኛ ቦታ ከነበረው ጀሞ ወደ መስቀል አደባባይ ለመዞር እንደተገደዱ ገልፀዋል። በቀጣይም በጥቂት ዓመታት ውስጥ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ተብሎ (105ሺህ ተሳታፊዎች በማሳተፍ) በጊነስ ቦክ ኦፍ ወርልድ ሪከርድ ከተመዘገቡት ውድድሮች ልቆ የመገኘት ትልም ስለመወጠኑም አቶ ይስማሸዋ ተናግረዋል፡፡

ክለቡ ከ12 እስከ 19 ሚልየን ብር ገቢ አገኝበታለሁ ብሎ እየተንቀሳቀሰበት በሚገኘው በዚህ ውድድር የክለቡ አጋር የሆነው ሀበሻ ቢራ በንጉስ ማልት ስም ውድድሩን ስፖንሰር የሚያደርግ ሲሆን በዕለቱ ለጊዜው ማንነቱ ያልተገለፀ የክብር እንግዳ በስፍራው እንደሚገኙም አቶ ይስማሸዋ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ታምራት በበኩላቸው በውድድሩ ዕለት ስለሚኖሩ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በንግግራቸውም በዕለቱ ከጠዋቱ 12 ጀምሮ ተሳታፊዎች በመስቀል አደባባይ በመገኘት መታደም የሚችሉ ሲሆን የዘንድሮ የሩጫ መነሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ” ቡናና ሻይ -ገነት ሆቴል-ቄራ-ጎተራ-አጎና ሲኒማ – መሿለኪያ በማድረግ መስቀል አደባባይ ላይ የሚጠናቀቅ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰለሞን አክለውም በቀኑ ከ150 በላይ አስተባባሪዎች የሚኖሩ ሲሆን በእለቱ ኢትዮጵያ ቡና አርማ ካረፈባቸው ቁሶች ውጪ ማንኛውም አይነት የተለየ ይዘት ያነገቡ ቁሶች ይዞ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ ስለመሆኑም አሳስበዋል፡፡

ሌላኛው የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ክፍሌ አማረ ለከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ምስጋናን አቅርበው በ4 የተለያዩ ቦታዎች የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በሚቀመጡባቸው የስታዲየም ክፍሎች ስያሜ በተሰየሙ ቦታዎች ላይ የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች ስለመኖራቸው ጠቁመዋል፡፡

በመቀጠል የ4ኛው ዙሬ የመሮጫ መለያውን ይፋ ያደረጉት አቶ ይስማሸዋ ሥዩም የዘንድሮው መለያ ከሌሎች ዓመታት የሚለየው የአሁኑ የመሮጫ መለያ በጀርባው ላይ ከ12 ቁጥር በተጨማሪ በደጋፊዎች ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል የሚታየው “ቡና ደሜ ነው” የተሰኘው መፈክር መታተሙ የተለየ እንደሚያደርገው ገልፀው ፤ ይህም መታሰቢያነቱ ለዘመናት ለዚህ ክለብ ደማቸውን ለሰጡ ደጋፊዎቻቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት መርሃግብሩ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡