የጣናው ሞገዶቹ የመጀመሪያ ተጨዋቻቸውን ሲያስፈርሙ የአንድ ተጫዋች ውል አድሰዋል

እስካሁን የአስር ነባር ተጨዋቾቻቸውን ውል ያደሱት ባህር ዳር ከተማዎች የመጀመሪያ ተጨዋቻቸውን ዛሬ ሲያስፈርሙ የመስመር ተከላካያቸውንም ውል ለማደስ ተስማምተዋል።

ፋሲል ተካልኝን ዋና አሰልጣኝ አድርገው የሾሙት ባህር ዳር ከተማዎች አዳዲስ ተጨዋቾችን ከማስፈረማቸው በፊት የነባር ተጨዋቾቻቸውን ውል ማደስ ላይ ተጠምደው የአስር ነባር ተጨዋቾችን ውል ማደሳቸው ይታወሳል። ትላንት ማምሻውን ደግሞ የጣናው ሞገዶቹ የመጀመሪያ ተጨዋቻቸውን በእጃቸው ማስገባታቸው ተረጋግጧል። ከሁለት ቀናት በፊት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተለያዩ ሁለት ወጣት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሳሙኤል ተስፋዬ የቀድሞ አሰልጣኙን ተከትሎ ወደ ባህር ዳር አምርቷል። ላለፉት ሁለት ዓመታት በዋናው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ቆይታ ያደረገው ተስፈኛው ተከላካይ በቀጣይ ለሁለት ዓመታት በባህር ዳር ቤት ለመቆየት ተስማምቷል።

ባህር ዳሮች አዲስ ካስፈረሙት ተጨዋች በተጨማሪ የመስመር ተከላካያቸውን ሳላምላክ ተገኝም ውል ለሁለት ዓመት አድሰዋል። በኢትዮጵያ ቡና የክለብ ህይወቱን የጀመረው ሳለአምላክ ተገኝ መጀመሪያ በውሰት ከዛም በቋሚነት በባህር ዳር ቤት አሳልፏል። የመስመር አማካይ እንዲሁም የመስመር ተከላካይ ሆኖ መጫወት የሚችለው ሳላምላክ በዓመቱ ወሳኝ ወሳኝ ጎሎችን ከተከላካይ መስመር እየተነሳ በማስቆጠር ቡድኑን ማገልገሉ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡