ፌዴሬሽኑ ከመመሪያ ውጪ የተጫዋቾችን ውል የሚያፈራርሙ ክለቦችን አስጠነቀቀ

(መረጃው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው )

በኘሪምየር ሊጉ ለሚጫወት ማንኛውም ተጨዋች ከነሐሴ 3 ቀን 2ዐ11 ዓ.ም ጀምሮ የደመወዙ ጣሪያ ታክስን ጨምሮ ብር 5ዐ,ዐዐዐ.ዐዐ (ሃምሳ ሺህ ብር) እንዲሆን 15 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቢሾፍቱ ላይ መወሰናቸው ይታወቃል፡፡ ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን እንዲያስፈጽም ክለቦች በወሰኑት መሰረት ፌደሬሽኑ በቁጥር 2/ኢ.እ.ፌ አ-4/1069 ነሐሴ 08/12/2011 ዓ.ም በጻፈው የሰርኩላር ደብዳቤ ክለቦች በዚህ ውሳኔ መሰረት የተጫወቾችን ውል እንዲፈጽሙ መግለጹ ይታወቃል፡፡

ሆኖም ግን የተወሰነውን ውሳኔ በአግባቡ ከመፈፀም ይልቅ የተወሰኑ ክለቦች በተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ውል እየተዋዋሉ እና እያፀደቁ በተቃራኒው ግብር የማይከፈልበት ገንዘብ በህገ-ወጥ መንገድ ለተጫዋቾች ክፍያ እየፈጸሙ እንደሆነ ከተለያዩ ጠቋሚ የመረጃ ምንጮች ጥቆማዎች ደርሰውናል፡፡

በመሆኑም ፌደረሽኑ ይህንን ህገ-ወጥ ድርጊት ከተጫዋቾች ጋር በመመሳጠር በታክስ ስወራና ህገ-ወጥ በሆነ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ ካላችሁ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እያሳሰብን፤ መንግስት በራሱ የሚወስደው እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ፌደሬሽኑም በዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርቶ በተገኘ ክለብ፤ የክለብ አመራርና ተጫዋቾች ላይ ከስፖርቱ ዓለም እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ዛሬ ለክለቦች በላከው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡