ወልቂጤ ከተማ ከዓለምአቀፍ የትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ነገ በይፋ ይፈራረማል

አዲስ አዳጊዎቹ ወልቂጤ ከተማዎች በሲንጋፖር መቀመጫውን ካደረገው ዓለማቀፉ የትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ “ማፍሮ ስፖርት” ጋር በነገው ዕለት በይፋ የትጥቅ አቅርቦት ውል ይፈራረማሉ፡፡

ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ እንደሆነ የተነገረለት የትጥቅ ማቅረብ ስምምነት በነገው ዕለት 10 ሰአት ላይ 22 አካባቢ በሚገኘው ብሉ ስካይ ሆቴል በሚደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፤ በመርሃግብሩ ላይም የወልቂጤ ከተማ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የማፍሮ ተወካዮችም እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለምስራቅ አፍሪካ ገበያ አዲስ ያልሆነው ማፍሮ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ትጥቅ አቅራቢ በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል። ድርጅቱ በቀጣይም በተለይ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ በስፋት ገብቶ የመስራት ውጥን እንዳለውም ለማወቅ ተችሏል ፤ ለዚህም አብረውት መስራት ለሚሹ ክለቦች የተሻለ አማራጮችን ይዞም ስለመምጣቱ ለማወቅ ችለናል፡፡

ወልቂጤ ከተማዎች ክለቡን አንድ እርምጃ ለማራመድ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን በቅርቡም በከፍተኛ ወጪ ያስገነቡትን አካዳሚ ለማስመረቅ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ