ወልቂጤ ከተማ | የአሰልጣኝ ደግአረግ ረዳቶች ታውቀዋል 

ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛውን ከቀጠረ በኋላ የአሰልጣኝ ስብስቡን ሙሉ ለማድረግ የረዳት አሰልጣኝ ፣ ግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እና ወጌሻ ቅጥር ፈፅሟል።

አዳነ ግርማ ወደ ወልቂጤ በተጫዋችነት እና ምክትል አሰልጣኝነት ለማምራት መቃረቡን ከዚህ ቀደም በሶከር ኢትዮጵያ መግለፃችን የሚታወስ ሲሆን አንጋፋው ተጫዋችም የአሰልጣኝ ደግአረግ ረዳት ለመሆን መስማማቱ ታውቋል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከባየር ሙኒክ ጋር በመተባበር ከመስከረም 5 ቀን ጀምሮ እያከናወነ በሚገኘው የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ አዳነ ግርማ እየተካፈለ ሲገኝ መጪውን የውድድር ዓመትም በተጫዋችነት እና ምክትልነት የምንመለከተው ይሆናል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ በግብ ጠባቂነት እና አሰልጣኝነት ረዘም ያለ ጊዜ ያሳለፈው በለጠ ወዳጆ የቡድኑ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል። በኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ሙገር ሲሚንቶ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ እና ትራንስ ተጫውቶ ያሳለፈው በለጠ በወልዲያ፣ መከላከያ፣ ሰበታ ከተማ እና መድን ግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ሲሰራ ቆይቷል።

በተያያዘ ዜና ወልቂጤ ጌታቸው ጋሻውን በወጌሻነት ቀጥሯል። ጌታቸው ከዚህ ቀደም በሰበታ፣ ሱልልታ እና ሆሳዕና ሲሰሩ ቆይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: