የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል

ከሁለት ሳምንታት በፊት በትግራይ ዓለማቀፍ ስታዲየም በሩዋንዳ 1-0 የተሸነፉት ዋሊያዎቹ የመልሱን ጨዋታ ነገ ያከናውናሉ።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2020 የቻን ውድድር ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ለመሳተፍ ነገ ወሳኝ 90 ደቂቃ ይጠብቀዋል። ይህንን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሩዋንዳ የተጓዘው ቡድኑም ትላንት እኩለ ቀን አካባቢ በስፍራው ከደረሰ በኋላ አመሻሹን ቀለል ያለ ልምምድ መስራቱ ታውቋል።

ቡድኑ ነገ ጨዋታው በሚደረግበት ሰዓት(11 ሰዓት) ልምምዱን ለ45 ያክል ደቂቃዎች ያክል በሪጅናል ኒያሚራምቦ ስታዲየም ማከናወኑ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በልምምድ መርሃ-ግብሩም ወደ ስፍራው የተጓዙ ሁሉም ተጨዋቾች በመልካም ጤንነት መገኘታቸው ታውቋል።

ባሳለፍነው እሁድ በዩጋንዳ 1-0 የተሸነፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚመሩት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ (ኢንስትራክተር) ከመረጡዋቸው 24 ተጨዋቾች ጀማል ጣሰው፣ ያሬድ ባዬ፣ አስቻለው ግርማ እና አህመድ ረሺድ በገጠማቸው ጉዳት ወደ ስፍረሰው እንዳልተጓዙ ይታወሳል።

ብሔራዊ ቡድኑ ኪጋሊ እንደደረሰ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ቡድናቸው ውጤቱን ቀልብሶ ወደ ውድድሩ እንደሚያመራ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ” የመጀመርያውን ጨዋታ በሜዳችን ተሸንፈናል። ሆኖም በቀሪው 90 ደቂቃ ለውጥ እንደምንፈጥር ትልቅ ተስፋ ሰንቀናል። በመጀመርያው ጨዋታ ያጣናቸው ሁለት ቁልፍ ተጫዋቾች ይዘናል። በመሠረቱ ጨዋታው ከባድ ይሆናል፤ ስለዚህ እስከጨዋታው እለት ጠብቀን የሚሆነውን መመልከት ነው። ” ብለዋል።

ጨዋታው ነገ በሪጅናል ኒያሚራምቦ ስታዲየም አመሻሽ 11 ሰዓት ይደረጋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ